ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፊሊፒንስ ማረሚያ ቤት ከምትገኘው እናት የተወሰደችው ህጻን ሞት ቁጣን ቀሰቀሰ
ፊሊፒንስ ውስጥ አንዲት የሶስት ወር ጨቅላ በማረሚያ ቤት ከምትገኘው እናቷ ከተለየች በኋላ ሕይወቷ ማለፉ የአገሬው ዜጋ በከፍተኛ ሁኔታ አስቆጥቷል።
ምንም እንኳን እናትየው ልጇ እና እሷ እንዳይነጣጠሉ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ሰሚ አላገኘችም ተብሏል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ ሪዬና ማይ ናሲኖ ባለፈው ዓመት ማኒላ ውስጥ በቁጥጥር ስር ስትውል ነፍሰ ጡር እንደሆነቸው ያላወቀች ሲሆን በመታሰሯ ጭንቀት ውስጥ ገብታ ስለነበር የወር አበባዋ መቅረቱን እንኳን እንዳላስተዋለችው ገልጻለች።
በማረሚያ ቤት ሆና በተደረገላት ምርመራ ነበር የ23 ዓመቷ ሪዬና ነፍሰ ጡር መሆኗን ያወቀችው።
የሪዬና የሶስት ወር ጨቅላ ከእናቷ ከተለየት ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ ነበር ባሳለፍነው ሳምንት ህይወቷ ያለፈው። በዚህም ምክንያት ፊሊፒንስ ውስጥ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ወላድ እናቶች በሚያገኙት እንክብካቤ ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል።
'ካዳማይ' ለሚባል በከተማ ድህነት ላይ በሚሰራ ድርጅት ውስጥ ትሰራ የነበረችው ሪዬና ባሳለፍነው ዓመት ህዳር ወር ላይ ነበር ቢሯቸው በፖሊስ ድንገተኛ እርምጃ ተወሰዶበት እሷ እና ሌሎች ሁለት ባልደረባዎቿ በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ሶስቱም ተጠርጠሪዎች በወቅቱ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝና ፈንጂ ቢሮ ውስጥ ማስቀመጥ የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። ነገር ግን ሁሉም ክሱን አንቀበለውም ጥፋተኞች አይደለንም በማለት ተከራክረዋል።
ምንም እንኳን የማረሚያ ቤት ሕይወት ከባድ ቢሆንም ሪዬና የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበልና ልጇን ለማሳደግ በደስታ እንደተቀበለችው ጠበቃዋ ጆዛሊ ዳኒኤላ ገልጻለች።
በአገሪቱ ሕግ መሠረት አንዲት ሴት በቁጥጥር ስር አያለች ልጅ ከወለደች ከአንድ ወር በኋላ እናትና ልጅ እንደሚለያዩ የሚደነግግ ሲሆን በአንዳንዳ አስገዳጅ ሁኔታዎች ግን ሌሎች አማራጮች ሊወሰዱ እንደሚችሉ ተቀምጧል።
በርካታ ፊሊፒንሳውያንም እናትና ልጅ በአፋጣኝ ከማረሚያ ቤቱ እንዲለቀቁ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ነበር።
የሪዬና እናትም ቢሆኑ በየሳምንቱ ምስሎችና ደብዳቤዎችን ለፍርድ ቤቱ በማሰገባት ልጃቸውና የልጅ ልጃቸው ከእስር እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ሪዬና ልጇን የተገላገለችበት ሆስፒታልም ቢሆን እናትና ልጅ ባይነጣጠሉ መልካም እንደሆነ የገለጸ ሲሆን የማረሚያ ቤቱ ባለስልጣናት ግን ይህንን ለማስፈጸም በቂ ግብአቶች እንደሌላቸው መግለጻቸውን ጠበቃዋ ተናግራለች።
ባለፈው መስከረም ወር ላይ የጨቅላዋ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱን ተከትሎ ወደ ሆስፒታል የገባች ሲሆን የጤናዋ ሁኔታ ግን እየተባባሰ መጥቷል። ይህንን ተከትሎም ነበር በርካታ ፊሊፒንሳውያን በአፋጣኝ እናትና ልጅ በድጋሚ አብረው እንዲሆኑ ጥያቄያቸውን ማቅረብ የጀመሩት።
ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ጨቅላዋ በሶስተኛ ወሯ በሳምባ ምች ሕይወቷ አልፏል። ህልፈተ ዜናዋም መላው ፊሊፒንሳውያንን አስደንግጧል። በርካሮችም በማህበራዊ ሚዲያ ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
ትናንት ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ፍርድ ቤት ሪዬና የልጇ ቀብር ላይ እንድትገኝ ከሶስት እስከ አራት ቀን ከማረሚያ ቤት እንድትወጣ ውሳኔ አስተላልፏል።