በሶማሌ ክልል የአዕምሮ ህመምተኛ ግለሰብ አራት የቤተሰብ አባላትን ገድሎ አምስቱን አቆሰለ

ታትሟል

በሶማሌ ክልል አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ ግለሰብ አራት የቤተሰብ አባላትን በመጥረቢያ ገድሎ፣ አምስቱን በከፋ ሁኔታ ማቁሰሉን ፖሊስ ገለፀ።

ጥቃቱ የደረሰው ፋፈን ዞን፣ ሃርሺን ወረዳ በምትባል የገጠር ቀበሌ ውስጥ ሲሆን ፤ ፖሊሶች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች የአዕምሮ ህመምተኛ ነው ያሉት ግለሰብ ዘጠኝ አባላት ያሉት ቤተሰብ ቤት ረቡዕ፣ መስከረም 27፣ 2013 ዓ.ም በመግባት ጥቃቱን ፈፅሟል ብለዋል።

ግለሰቡ ጥቃቱን ከማድረሱ በፊት መጥረቢያ ይዞ በአካባቢው ይዘዋወር የነበረ ሲሆን የአካባቢው ፖሊስ የቅርብ ዘመድ ናቸው ያላቸው ቤት ውስጥ ገብቶም ባል፣ሚስትና ሁለት ልጆችን የገደለ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በአምስቱ ልጆቻውም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንዳደረሰባቸው ከአካባቢው የተገኘው ፖሊስ መረጃ ጠቁሟል።

በመጥረቢያም ጭንቅላታቸው፣ ሆዳቸውና እግራቸውን እንደመታቸውና ለከፋ ጉዳትም ተጋልጠዋል ተብሏል።

የሞቱት የቤተሰቡ አባላት የተቀበሩ ሲሆን፤ የቆሰሉት አምስቱ ልጆች ወደ ጂግጂጋ ሪፈራል ሆስፒታል መላካቸው ተገልጿል።

ቢቢሲ ሶማሊ ከሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎችን ጠይቆ ባጠናቀረው መረጃ መሰረት ጂግጂጋ ሪፈራል ሆስፒታልም ቀዶ ህክምና የተደረገላቸውም ሲሆን በኮማ ውስጥ ናቸው ተብሏል።

ግለሰቡ ለረዥም አመታትም በአዕምሮ ህመምተኛነቱ የሚታወቅ ሲሆን ግለሰቡ የቤተሰቦቹ የቅርብ ዘመድ በመሆኑም በቀላሉ ወደቤት ሊገባ እንደቻለና ጥንቃቄም አለማድረጋቸውንም ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከዚህ ቀደምም ወደቤታቸው መጥቶ ምግብም፣ መጠጥም እንዲሁም አንዳንድ ድጋፎች ያደርጉለት የነበረ በመሆኑም ጥርጣሬ እንዳልነበራቸው ፖሊስ አሳውቋል።

ፖሊስ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ግለሰቡ ለረዥም ጊዜ የአዕምሮ ህመምተኛ እንደነበር ገልፀው፤ በተደጋጋሚም ሐረር፣ ጅጅጋና በአካባቢው ባሉ የጤና ህክምና ማዕከሎችም ህክምና በተደጋጋሚ ያደርግ ነበር። ለተወሰነ ጊዜም በሰንሰለት አስረውት እንደነበርና በከፍተኛ ሁኔታ የጤና መቃወስም ደርሶበት ነበር ተብሏል። እስካሁንም ድረስ ሰው ላይ ጥቃት የማድረስ ሁኔታ አልነበረውም ብለዋል።

ግለሰቡ ጥቃቱን ካደረሰ በኋላ ለማምለጥ ቢሞክርም ፖሊስ አሰሳ አድርጎ በቁጥጥር ስር እንዳዋለውም መረዳት ተችሏል።

የሃርሺም ወረዳ ፖሊስ፣ ለዞን ፖሊስ በማስተላለፍ፣ ዞኑም ወደ ክልሉ ፖሊሰ ግለሰቡን አሳልፎ የሰጠው ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በጂግጂጋ ከተማ በክልሉ ፖሊስ ቁጥጥርም ስር ይገኛል።

የፖሊስ ኃላፊዎች እንደገለፁት ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ወደ ህግ ለማቅረብ ምርመራ እያደረጉ ነው።