የሕዝብ ንብረት ለፓርቲ ጥቅም ያዋሉት ሚንስትር የ3 ወር ደመወዝ ተቀጡ

ታትሟል

የደቡብ አፍሪካ አየር ኃይል አውሮፕላንን ለፓርቲ ጥቅም አውለዋል የተባሉት የመከላከያ ሚንስትር የሦስት ወር ደመወዛቸውን ተቀጡ።

ኖሲቪዌ ማፒሳ-ናቃኩላ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ አመራሮች የአየር ኃይሉን አውሮፕላን ተጠቅመው ወደ ዚምባብዌ እንዲሄዱ ፈቅደዋል ተብሏል።

በዛ ጉዞ ላይ ሚንስትሯም አብረው ተጉዘው እንደነበረ ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሚንስትሯን የሦስት ወር ደመወዝ ከቀጡ በኋላ ገንዘቡ የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ለሚደረገው እንቅስቃሴ ገቢ እንዲሆን አዘዋል።

የመከላከያ ሚንሰትሯ ቢሮ ግን ኖሲቪዌ ማፒሳ-ናቃኩላ ለሥራ ጉዳይ ወደ ዚምባበዌ ሲሄዱ ለተቀሩት የፓርቲ አመራሮች እግረ መንገዳቸውን እንዲሳፈሩ ፈቀዱ እንጂ ጉዞ ለፖለቲካ ሥራ አልነበረም ሲል አስተባብሏል።

የሚንስትሯ ቢሮ ኖሲቪዌ ማፒሳ-ናቃኩላ ወደ ሐራሬ የተጓዙት በቀጠናዊ ጉዳይ ላይ ለመምከር ነው ብሏል።

የደቡብ አፍሪካው ገዢ ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ አመራሮች ደግሞ ከዚምባብዌ አቻቸው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ አመራሮች ጋር በዚምባብዌ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ጉዳይ ላይ ለመምከር ወደ ሐራሬ ማቅናታቸው ተጠቅሷል።

ፕሬዝደንት ራማፎሳ ግን የሚንስትሯን ተግባር ስህተት ነው ብለውታል።

ፕሬዝደንቱ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ገዢውን ፓርቲ እና ባለስልጣናትን ከተዘፈቁበት ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንደሚያላቅቁ ቃል ገብተው ነበር።

"የሚኒስትሯ ተግባር ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚቃረን ነው" ካሉ በኋላ የሦስት ወር ደመወዝ ለመቅጣት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም የሚንስትሯን ተግባር አጥብቀው ኮንነዋል። ፕሬዝደንቱ የወሰዱት እርምጃም በቂ አይደለም እያሉ ነው።