የማሊ መፈንቅለ መንግሥት፡ ወታደራዊ መሪዎች ለ18 ወራት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ተስማሙ

ታትሟል

በማሊ ባለፈው ወር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ወታደራዊ መሪዎች ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ለ18 ወራት የሚቆይ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም መስማማታቸው ተገለፀ።

ቃል አቀባዩ ሞሳ ካማራ እንዳሉት ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥቱ በወታደራዊ መኮንን አሊያም በሲቪል ይመራል ብለዋል።

እዚህ ስምምነት ላይ የተደረሰው ማሊ ወደ ሲቪል አገዛዝ የምትመለስበት የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተ ከተቃዋሚ እና የማህበረሰብ ስብስብ ቡድኖች ጋር ለሦስት ቀናት ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው።

መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች ወደ ሲቪል አገዛዝ ስርዓት መመለስ አለባት ሲሉ ተናግረው ነበር።

የማሊ አዲሱ ወታደራዊ መንግሥትም ቀደም ሲል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥቱ ለ2 ዓመታት እንዲቆይ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጅ ከውይይቱ በኋላ የወታደራዊ ቡድን መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ፤ ለማሊ ሕዝብ ጥቅም ሲባል ስምምነቱን እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።

ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞ ፕሬዚደንቱ ኢብራሂም ባውባካር ኬታ መጀመሪያ ላይ በወታደራዊው ኃይል በቁጥጥር ስር ውለው ታስረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ተለቀዋል፤ ከአገር የወጡትም ባለፈው ሳምንት ነበር።

የ75 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዚደንቱ፤ መጠነኛ የደም ዝውውር መታወክ [ስትሮክ] ካጋጠማቸው በኋላ ከስምንት ቀናት በፊት ለሕክምና ወደ ተባባሩት አረብ ኤምሬቶች መሄዳቸውን ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የፕሬዚደንቱ የቀድሞ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ለ15 ቀናት ያህል እዚያ ሊቆዩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ኬታ በአገሪቷ ውስጥ ያለውን ሙስና፣ የምጣኔ ሐብት ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍልና አወዛጋቢ ምርጫን በተመለከተ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ከሥልጣን የተወገዱት ከአንድ ወር ገደማ በፊት ነበር።

መፈንቅለ መንግሥቱ ዓለም አቀፉ ውግዘትን ያስከተለ ቢሆንም በርካታ ማሊያዊያንን ግን አስፈንድቆ ነበር።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ከ60 ዓመታት በፊት ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ከተላቀቀች በኋላ መፈንቅለ መንግሥት ሲካሄድ ይህ አራተኛው ነው።

ከ8 ዓመታት በፊት በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋትም እስላማዊ ታጣቂዎች የሰሜናዊ ማሊን ግዛት እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸው ነበር።

የፈረንሳይ ወታደሮች ግዛቷ እንድትመለስ ድጋፍ ቢያደርጉም፤ አሁንም ግን ጥቃቶች እንደቀጠሉ ነው።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎችም ጂሃዲስትን ለመዋጋት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማክበር ቃል ገብተዋል።

ታጣቂዎቹን ለመዋጋትም በሺዎች የሚቆጠሩ ፈረንሳዊያን ፣ አፍሪካዊያን፣ እና የተባበሩት መንግሥታት ወታደሮች በአገሪቷ ውስጥ ይገኛሉ።