እውቁ የኖቤል አሸናፊ የግድያ ዛቻዎች እየደረሳቸው መሆኑ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto
የ2018ቱን የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ዶ/ር ዴኒስ ሙክዌጌ ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎች እየደረሷቸው መሆኑ ተነገረ።
ሃኪሞች ለሰብዓዊ መብቶች (ፒኤችአር) የተሰኘው ቡድን እንዳስታወቀው፣ ኮንጎዋዊው ሃኪም ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻ እየደረሳቸው ስለሆነ የተባበሩት መንግሥታት ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባል ብሏል።
ዶ/ር ዴኒስ ከሁለት ዓመት በፊት የሰላም የኖቤል ክብርን ያገኙት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በማከማቸው ነው።
የሰብዓዊ መብት ተከራካሪው ቡድን እንደሚለው ከሆነ ዶ/ር ሙክዌጌ "አሳሳቢ በሆነ መልኩ የጥቃት ኢላማ የሚያደርጋቸው ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል።"
በእጅ ስልካቸው ላይ ጭምር የግድያ ዛቻ እየደረሷቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
የጤና ባለሙያው ላይ መሰል የግድያ ዛቻ እየደረሰ ያለው፤ በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ እአአ ከ1993 እስከ 2003 ባሉት ዓመታት በሰዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥስት የፈጸሙት ቡድኖች ላይ ጥብቅ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ መወሰድ አለበት በማለት ቅስቀሳ በማድረጋቸው መሆኑን ፒኤችአር የተሰኘው ቡድን አስታውቋል።
ሕምሌ ወር ላይ የቀድሞ የሩዋንዳ መከላከያ ሚንስትር ጀነራል ጄምስ ካባሬቤ በሩዋንዳ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ዶ/ር ሙክዌጌን አጥብቀው ኮንነዋል። የቀድሞ መከላከያ ሚንስትር "የሩዋንዳ ጦር በኮንጎ ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል እያሉ ሃሰተኛ ወሬ ከሚያስራጩት መካከል ዶ/ር ሙክዌጌ አንዱ ናቸው" ብለዋል።
ሃኪሞች ለሰብዓዊ መብቶች (ፒኤችአር) ቡድን በዲሞክራቲ ሪፓብሊክ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ለዶ/ር ሙክዌጌ እና እርሳቸው ለሚሰሩበት ሆስፒታል መላው ሰራተኛ ከለላ እንዲሰጥ ጠይቋል።
ዶ/ር ሙክዌጌ በኮንጎዋ ቡካቩ ከተማ የሕክምና ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።















