ኮሮናቫይረስ፡ በአሜሪካ አንዲት ነብር ኮሮናቫይረስ ተገኘባት

ታትሟል

አራት ዓመት ዕድሜ ያላትና የማላየን የነብር ዝርያ የሆነች "ታይገር" አሜሪካ ውስጥ በኮቪድ-19 ቫይረስ ተጠቂ እንደሆነች በምርመራ ተረጋገጠ።

በኒው ዮርክ ከተማ ብሮኒክስ መካነ-እንሰሳት ውስጥ ነዋሪ የነበረችው የነብር ዘር በኮሮናቫይረስ ተጠቂ ስለመሆኗ የአይዋ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት ላቦራቶሪ አረጋግጧል።

ናዲያ የሚል ስም የተሰጣት ይቺ የነብር ዘር እህቶቿን ጨምሮ ሁለት አሙር ታይገሮች እንዲሁም ሦስት የአፍሪካ አናብስት ከሰሞኑ በተመሳሳይ ደረቅ ሳል ምልክት ሲያሳዩ ነበር።

አሁን ግን ሁሉም በማገገም ላይ ናቸው ተብሏል።

ናዲያ የተባለችው የነብር ዝርያ ምናልባትም ከመካነ-እንሰሳቱ ጠባቂ ቫይረሱ እንደተጋባባት ጊዜያዊ ግምት ተወስዷል።

የዚህ የኒውዮርክ የእንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ባወጣው መግለጫ "ነብሯ" ላይ ምርመራ የተደረገው በጠቅላላ በኒው ዮርክ ካላው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ሲሆን እነሰሳት ላይ የሚደረገው ምርመራ ለጠቅላላው የኮቪድ-19 ጥናትና ምርምር ትልቅ ግብአት ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ገልጿል።

የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ኮሮናቫይረስ በሰው ልጆች በሚስፋፋው መጠን በዱር እንሰሳት መሀል በስፋት የሚሰራጭ ከሆነ አካባቢንና ተፈጥሮን እንዳያመናምን ከፍተኛ ስጋት ገብቷቸዋል።