ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የመንግሥት ኃላፊዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲዘጋጁ ጠየቀ
ታትሟል
የኢትዮጵያዊያን የአኗኗር ዘዬ ለኮሮናቫይረስ በቀላሉ መሰራጨት ምቹ በመሆኑ ምዕመናን ይህን ልማድ ለጊዜው በመግታት የጤና ተቋማት የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።
ጉባኤው ምዕመናን የቫይረሱ ምልክቶችን በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ ሲመለከቱ መረጃውን በአፋጣኝ ለሚመለከታቸው የጤና ተቋማት እንዲያሳውቁም ጠይቋል።
ምዕመናን በየቤተ እምነታቸው ተገኝተው የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶችን ሲካፈሉም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፤ ይህንንም ሲያደርጉ የሌሎችን ስሜትና ሥነ ልቦና በማይጎዳ መልኩ እንዲሆን አሳስቧል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው።
በሌላ በኩል የንግድ ማኅበረሰቡም የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚያስፈልጉም ሆነ በሌሎች የፍጆታ እቃዎች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ ከማድረግ እንዲታቀቡም ጠይቋል።
የመንግሥት ኃላፊዎች አስፈላጊውን ጥረትና ዝግጅት እንዲያደርጉ፤ መገናኛ ብዙሃንም ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ በማድረስ ወገናቸውን የመርዳት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስቧል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ።