የፔሌ ጤንነት እያሽቆለቆለ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
የስመ ገናናው የእግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ የጤንነት ሁኔታው በማሽቆልቆሉና ያለ ደጋፊ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ የተነሳ ከቤቱ ለመውጣት ፈቃደኛ አለመሆኑን ልጁ ተናገረ።
የሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ፣ በስፋት የምንግዜም ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የሚንቆለጳጰሰው ፔሌ ባለፈው ዓመት ወደ ሆስፒታል የተወሰደው በሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ምክንያት ነበር።
የ79 ዓመቱ ፔሌ ከዚህ ቀደም ጭኖቹ ላይ ችግር የነበረበት ሲሆን በዚህም የተነሳ በድጋፍ ለመንቀሳቀስ ተገዶ ነበር። ከቅርብ ጊዜያትም ወዲህም ወደ ህዝብ በቀረበባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖ ሲንቀሳቀስ ታይቶ ነበር።
ልጁ ለግሎቦ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገረው ከሆነ "በጣም በራስ መተማመኑ ቀንሷል፤ እንዲህ ሆኖ ማንም እንዲያየው ስለማይፈልግ ከሰው ጋር አይገናኝም" ብሏል።
ፔሌ በዓለም ክብረወሰን የተመዘገበለት 1,281 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን በ21 ዓመት የተጫዋችነት ዘመኑ 1,363 ጊዜ በጨዋታ ላይ ተሳትፏል።
እንዲሁም ለብራዚል በተሳተፈባቸው 91 ጨዋታዎች 77 ጎሎችን ያስቆጠረ ምርጥ ተጫዋች ነበር።
የፔሌ የጤንነት ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ሲሆን በ2015 የፕሮስቴት ቀዶ ህክምና አድርጓል። በወቅቱ በተደጋጋሚ ወደ ሆስፒታል የሄደ መሆኑም ይታወሳል።
"ልብ በሉ፤ ንጉሥ ነው፤ ምን ጊዜም ተጽዕኖ ፈጣሪ፣ ተምሳሌት የሚሆን ነው፤ ዛሬ ግን በአግባቡ መራመድ አይችልም" ብሏል ልጁ ለቴሌቪዥን ጣቢያው።
"በጣም በአስጊ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፤ ዳሌው ላይ ቀዶ ጥገና አድርጎ ነበር፤ በአግባቡ የማገገሚያ ሕክምና አልወሰደም። ስለዚህ መንቀሳቀስ ላይ ይቸገራል፤ ያ ደግሞ የራሱ የሆነ ድብታ ፈጥሮበታል" ብሏል።













