ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮንጎ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ከቀብር ሲመለሱ ከነበሩት 15ቱ ሞቱ
ታትሟል
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በጀልባ መገልበጥ አደጋ ቢያንስ 15 ሰዎች ሞቱ።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምዕራባዊ አካባቢ በሚገኝ ሐይቅ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸውን ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል የአካባቢውን ከንቲባ ጠቅሶ ዘግቧል።
በማይ ንዶምቤ ሐይቅ ባሳለፍነው ሰኞ በደረሰው በዚህ አደጋ በርካታ ሰዎች መጥፋታቸውም ታውቋል።
ጀልባዋ ከከተማዋ 35 ኪሎ ሜትር ከሚርቅ ሥፍራ ከቀብር ሥነ ሥርዓት በመመለስ ላይ የነበሩ 30 የሚሆኑ ሰዎችን አሳፍራ ነበር።
የአደጋው ምክንያት አልታወቀም።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር 400 ሰዎችን አሳፍራ የነበረች ጀልባ በዚሁ ሐይቅ ሰምጣ ቢያንስ 45 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
አብዛኞቹ ደመወዛቸውን ለመቀበል ለመሄድ ተሳፍረው የነበሩ መምህራን ነበሩ።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጀልባዎች ከአቅም በላይ በመጫናቸውና በቂ ጥገና ስለማይደረግላቸው ተመሳሳይ አደጋ በተደጋጋሚ ያጋጥማል።