በፓራጓይ 75 እስረኞች ወደሰማይ ይትነኑ ወደ ምድር ይስረጉ ባልታወቀ ሁኔታ ጠፉ

ታትሟል

በላቲን አሜሪካዋ አገር ፓራጓይ 75 እስረኞች ወደሰማይ ይትነኑ ወደ ምድር ይስረጉ ባልታወቀ ሁኔታ መጥፋታቸው አወዛጋቢ ሆኗል።

ብዙዎች የአገሪቱ ባለስልጣናት በአንድ ነገር ላይ የተስማሙ ይመስላሉ። የጥበቃ ሰዎች እስረኞቹ እንዲወጡ አድርገዋቸው በሚል። ሌላም ሌላም ነገር ተብሏል። እውነታው ግን ከዚያ የተለየ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ ክሱ የቀረበባቸው የጥበቃ ሰራተኞች ናቸው።

በብራዚል ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው በዚህ እስር ቤት ጠባቂዎች በበር ያስወጡት አንድም ታሳሪ አለመኖሩን ይገልጻሉ። ታዲያ እስረኞቹ በየት በኩል ወጡ? ይህ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ቢመስልም የአገሪቱ ባለስልጣናት ግን እስረኞቹ በበር መውጣታቸውን ነው የሚያረጋግጡት። እንዴት? ይህም መልስ የሚያሳፈልገው ሌላ ጥያቄ ነው።

ባለስልጣናቱ የጥበቃዎቹን ሴራ ለመደበቅ የተዘጋጀ ማደናገሪያ ነው ቢሉትም በእስር ቤቱ ውስጥ የጠፉት ታራሚዎች ምናልባት አምልጠውበት ሊሆን ይችላል የተባለ ጥልቅና ረጅም ቱቦ ተገኝቷል።

ካመለጡት ታሳሪዎች መካከል በርካቶቹ ብራዚል ውስጥ የሚገኝ የዝርፊያ ቡድን አባል ናቸው ተብሏል።

30 ሺህ አባላት ያሉት ይህ የዝርፊያ ቡድን መቀመጫውን ብራዚል ሳኦ ፖሎ ያደረገ ሲሆን በዕጽና መሳሪያ ዝውውር ውስጥ በስፋት የተሰማራ ነው። በብራዚል፣ ፓራጓይ፣ ቦሊቪያና ኮሎምቢያ ውስጥ በስፋት ይንቀሳቀሳል። የገንዘብ አቅሙም ፈርጠም ያለ ስለሆነ አባሎቹን ለማስፈታት ሁሉንም አማራጭ ሊጠቀም እንደሚችል ይጠበቃል።

እሁድ ዕለት በምሥራቃዊ ፓራጓይ ውስጥ የሚገኘው እስር ቤት ሲመረመር ከዘራፊ ቡድኑ አባላት መካከል የተገኘ ታራሚ አልነበረም። ሁሉም ወደሰማይ ይትነኑ ወደ ምድር ይስረጉ ባልታወቀ ሁኔታ እነሱ የሚቆዩበት ክፍል ኦና ሆኖ ተገኝቷል።

በአንደኛው የእስር ቤቱ ክፍል ውስጥ ደግሞ 200 የሚሆኑ በአሸዋ የተሞሉ ዶንያዎች ተከማችተው ተገኝተዋል። ምናልባትም ይህ የአፈር ክምር ቱቦው ሲዘጋጅ ከውስጥ ተቆፍሮ የወጣ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አድሯል። በዚህ ቅጽበትም አንድ እስረኛ በተዘጋጀው ቱቦ ሊያመልጥ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉ ጥርጣሬውን እውነት ሊያደርገው ይችላል ቢባልም ባለስልጣናቱ ግን አይቀበሉትም።

ባለስልጣናቱ እስረኞቹ በቱቦው መውጣታቸውን አያምኑም። የአገሪቱ ሹማምንት እንደሚሉት እስረኞቹ ያመለጡት ልክ እንደማንኛውም ሰው ዘና ብለው እተሳሳቁና ጓደኞቻቸው ጋር ተቃቅፈው በበር በኩል ነው።

የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚንስትር የተቆፈረው ቱቦ ወንጀሉን ለመሸፋፈን የተደረገ እንጂ የጠፉት ታሳሪዎች እንደሆኑ በጥበቃዎቹ ረዳትነት በበር በኩል ነው የወጡት ይላሉ።

ይህ የሆነው ደግሞ የእስር ቤቱ ዋና አዛዥ ለአመታዊ እረፍት በወጡበት ወቅት ነው።

የፍትህ ሚንስትርም የአገር ውስጥ ሚንስትሩን ሃሳብ ያረጋግጣል። ለጥበቃዎቹ 80 ሺህ ዶላር ወይም 2.4 ሚሊዮን ብር አካባቢ ገንዘብ አፍ ማዘጊያ ተሰጥቷቸው በበር ነው እንዲወጡ የተደረገው ብሏል ፍትህ ሚንስቴሩ መግለጫ።

ከእስር ቤቱ አምልጠዋል የተባሉት የዘራፊ ቡድኑ አባላት አብዛኛዎቹ ብራዚላዊያን ናቸው። ከእስር እንዳመለጡ ድንበር አቋርጠው ወዳገራቸው ተሻግረዋል ተብሏል። ይህም የተረጋገጠው ድንበር አካባቢ የተጓዙበትን ተሽከርካሪ አቃጥለው በመሰወራቸው ነው ተብሏል። ባለስልጣናቱና የበር ጠባቂዎች እርስ በርስ ቢካሰሱም እስረኞቹ በየት በኩል አመለጡ የሚለው ግን አሁንም ተጨማሪ ማጣሪያ የሚያስፈልገው ይመስላል።

አካባቢው ሕገ ወጥ የዕጽ ዝውውር ገበያ የሚደራበት ነው።