የአሳማ በሽታ ወረርሽኝ ኢንዶኖዥያን ስጋት ውስጥ ከቷታል

ታትሟል

ኢንዶኖዠያ 'አፍሪካን ስዋይን ፊቨር' በሚባልና አሳማዎችን በሚያጠቃው የቫይረስ በሽታ የተቸገሩ ሀገራትን ተርታ ተቀላቅላለች።

ገዳይ የሆነው የአሳማው በሽታ በአገሬው አርሶአደሮች ላይ ፍርሃትን አንግሷል።

ረቡዕ ዕለት ያገሪቱ የግብርና ሚኒስትር እንዳሳወቁት 30 ሺ የሚጠጉ አሳማዎች በሰሜናዊ ሱማትራ በምትገኘው ግዛት በበሽታው ሞተዋል።

ቫይረሱ የቻይናን ከግማሽ በላይ የሚያሆን የአሳማ መንጋ ከምድረ ገጽ ያጠፋል ተብሎ ይገመታል። አውስትራልያ ካሁኑ በሽታውን በመፍራት የስነ ሕወታዊ ደህንነት ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።

እንደ የአለም የእንስሳት ጤና ድርጅት መረጃ ምንም እንኳን በሽታው ሰዎችን የሚጎዳ ባይሆንም በቀናት ውስጥ አሳማዎችን ይገድላል። የመግደል አቅሙ ደግሞ መቶ በመቶ የተረጋገጠት ነው ተብሏል።

ቫይረሱ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ለሰባት ቀናት ያለ ተሸካሚ መቆየት የሚችል ሲሆን በረዶ ውስጥ በተቀመጠ የአሳማ ስጋ ውስጥ እንኳን ለወራት መቆየት ይችላል።

የትኞቹ ሃገራት በሽታው ተጋርጦባቸዋል?

ትልቁ ችግር ያለው አሁን ቻይና ላይ ነው፤ የበሽታው ስርጭት ግን ደቡባዊ ምስራቅ እስያን እያሸበረ ነው ያለው። ቪየትናም እና ፊሊፒንስ በክልሉ የከፋ ስርጭት ታይቶባቸዋል ተብሏል።

ታዋቂው የሆላንድ ድርጅት ራቦባንክ ተንታⶉች እንዳሉት በዚህ ዓመት ቪየትናም 21 በመቶ የአሳማ ስጋ ምርት እጥረት የሚያጋጥማት ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 8 በመቶ ይሆናል ብሏል።

በ 2020 የፊሊፕንስ የአሳማ መንጋ በ13% ይቀንሳል ተብሏል። በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያትም ቻይና ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአሳማ መንጋዋን ታጣለች።

አውስራልያ በስነ ሕይወታዊ ደህንነት መከላከል ስራ ላይ በምትወስደው ጠንቃቃ እርምጃ ትታወቃለች። ለምታካሄደው ቫይረሱን የማጥፋት ስራም ተጨማሪ 45 ሚልዮን ዶላር መድባለች። ነገር ግን አሁን ያጋጠማት ሁኔታ ስራውን ሳያከብድባት አይቀርም።

ባለፉት ስድስት ወራት የአውስትራልያ ባለስልጣናት 32 ቶን የአሳማ ስጋ ምርቶችን ከመንገደኞች ሻንጣ እና ከመልእክት ሳጥኖች ውስጥ በመያዝ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርገዋል።

"ከተያዙት ውስጥ 49 ከመቶዎቹ የአፍሪካው የአሳማ በሽታ ተገኝቶባቸዋል" ብለዋል ማርጎ አንድሬ የተባሉት የአውስትራልያ የአሳማ ስጋ ኩባንያ ሃላፊ።

የአውስትራልያ የአሳማ ኩባንያ የመጣው በሽታ በዘርፉ ላይ የ 2 ቢልዮን ዶላር የገበያ እጥረት ሊፈጥር ይችላል ሲል ይገምታል። ይህም 5.3 ቢልዮን የአውስትራልያ ዶላር ሲሆን 36ሺ ሰራተኞችን የሚያስተዳድር ነው።

ጀርመን ደግሞ የፖላንድ ድንበር አካባቢ የዱር አሳማ ላይ ቫይረሱ ከተገኘ በኋላ ሽታውን ለማቆም የምታደርገውን እንቅስቃሴ ጀምራለች።

አሜሪካ የአፍሪካ አሳማ በሽታ አላጋጠማትም። ሆኖም ባለስልጣኖች የእንስሳት ጤናን እየከታተላሉ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች ላይ ከባድ ቁጥጥር እኣደረገች ትገኛለች።