ጣልያን ውስጥ አራት ሕንዳውያን አዛባ ውስጥ ሰጥመው ሞቱ

ታትሟል

አራት ሕንዳውያን፤ የቀንድ ከብት አዛባ በሚጠራቀምበት ሰፊ ታንከር ውስጥ ሰጥመው ሕይወታቸው አለፈ።

በሰሜን ጣልያን በሚገኝ የወተት ምርት ማቀነባበርያ ድርጅት ውስጥ ባለ ታንከር ውስጥ አንድ ግለሰብ ከገባ በኋላ፤ ሕይወቱን ለማትረፍ አዛባ ወደሞላው ታንከር ውስጥ ዘለው የገቡት ሦስት ሰዎች ሞተዋል።

የመጀመሪያው ግለሰብ ወደ ታንከሩ የገባው ለጽዳት ነበር።

ሟቾቹ ሕንዳውያን 28፣ 29፣ 45 እና 48 ዓመታቸው ነበር። አራቱ ግለሰቦች ጉድጓዱ ውስጥ በካርቦን ዳይኦክሳይድ ታፍነው እንደሞቱ አስከሬኑን የመረመሩት ባለሙያዎችተናግረዋል።

ሟቾቹ ምሳ ሰዓት ላይ እንደወትሯቸው ወደየቤታቸው አለመሄዳቸውን ተከትሎ፤ የያንዳዳቸው ባለቤቶች ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አስታውቀዋል። የቀንድ ከብቶች አዛባ የሚጠራቀምበት ታንከር በእሳት አደጋ ተከላካዮች ከተጸዳ በኋላ የሟቾቹ አስክሬን ተገኝቷል።

ማቀነባበሪያው ውስጥ የሚጠራቀመው የቀንድ ከብቶች አዛባ ለማዳበሪያነት ይውላል።

የጣልያን መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት፤ ባለፉት ወራት በሥራ ሥፍራ በደረሰ አደጋ 486 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።