ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይኛ ያልተጠቀመው አየር መንገድ ሊቀጣ ነው
የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ጥንዶችን መብት ጥሷል የተባለው ኤር ካናዳ ለጥንዶቹ 15,700 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ታዟል። የካናዳው አየር መንገድ ለጥንዶቹ የይቅርታ ደብዳቤ እንዲጽፍም ተወስኖበታል።
ጥንዶቹ አየር መንገዱን የከሰሱት አውሮፕላን ውስጥ ያሉ ምልክቶች የተጻፉት በእንግሊዘኛ ብቻ ነው ብለው ነበር። በፈረንሳይኛ የተጻፈ መግለጫ ባለበት አካባቢ ደግሞ ከእንግሊዘኛው እኩል ዋጋ አልተሰጠውም ሲሉም ጥንዶቹ ተናግረዋል።
ሚሼል ቲቦዴው እና ሊንሳ ቲቦዴው የተባሉት ጥንዶች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2016 ኤር ካናዳ ላይ 22 ክስ አቅርበዋል።
ጉዳዩን የመረመሩት የኦቶዋ ዳኛ፤ ካናዳ ኤር በሁለት የሥራ ቋንቋ የመሥራት ሕግን ተጻሯል ብለዋል። አየር መንገዱም መልዕክቶችን በእንግሊዘኛ ብቻ ሳይሆን በፈረንይኛም እንደሚጽፍ ቃል ገብቷል።
ጥንዶቹ እንዳሉት ከሆነ አውሮፕላን በረራ ከመጀመሩ በፊት የሚሰጠው የእንግሊዘኛ ማብራርያ ከፈረንሳይኛው በበለጠ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘ ነው።
በካናዳ ሕግ መሰረት፤ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ እኩል ቦታ ተሰጥቷቸው ጥቅም ላይ መዋል ያለባቸው ቋንቋዎች ናቸው።
ጥንዶቹ አየር መንገዱ እንዲቀጣ በመወሰኑ ደስ እንዳላች ገልጸው፤ ለወደፊት በቋንቋ ረገድ የተሻለ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።