ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጠፉት ታይላንዳውያን ልጆች በዋሻ ውስጥ ለወራት ሊቆዩ ይችላሉ
ከሳምንት በላይ ጠፍተው የነበሩት 12 ታይላንዳውያን ወንዶች ልጆችና አሰልጣኛቸው በታይላንድ ዋሻ ውስጥ በህይወት እንዳሉ ታውቋል።
ዋሻው በጎርፍ በመሞላቱ ጎርፉ እስኪቀንስ ለወራት መጠበቅ፤ ወይም ደግሞ ዘለው በዋና ሊወጡ እንደሚገባም ተገልጿል።
ልጆቹና አሰልጣኛቸው ለዘጠኝ ቀናት ያህል ያሉበት ባለመታወቁ ጠፍተዋል ተብለዋል ተብሎ የነበረ ሲሆን፤ ሰኞ አመሻሹ ላይ ፈላጊዎች በዋሻው ክፍተት በኩል አይተዋቸዋል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶችም ለማድረስ በመታገል ላይ ናቸው።
ቢያንስ ለሚቀጥሉት አራት ወራት ያህልም ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ሰራዊቱ ገልጿል።
ልጆቹን ለመፈለግ የተቋቋመው ቡድን አባል የሆኑት ሁለት የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው የአደጋ ሰራተኞች ናቸው ልጆቹን ያገኟቸው።
ልጆች ጎርፍ በተሞላው ዋሻ አጠገብ በሚገኝ አፋፍ ተቀምጠው የታዩ ሲሆን ሁሉም የቡድኑ አባላት በህይወት እንዳሉና በጣም እንደተራቡም ገልፀዋል።
ምንያህል ጊዜ በዋሻው ውስጥ እንደቆዩና አሁን መመለስ ይችሉ እንደሆነ የጠየቁ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቸም በምላሹ መጠበቅ እንዳለባቸውና ሌሎች ሰዎችም እንደሚመጡ ገልፀውላቸዋል።
አንደኛውም ልጅ "እሺ ነገ እንገናኛለን" የሚል ምላሽም ሰጥቷል።
በህይወት መኖራቸው ግልፅ ያልነበረ ሲሆን ፍለጋውንም ብዙዎች በጉጉት ሲከታተሉት ነበር።
የጠፉት ልጆች ቤተሰቦች መገኘታቸውን ሲሰሙ ደስታቸውንም በከፍተኛ ሁኔታ ገልፀዋል።
ዋሻው የሚገኝበት ሰሜናዊ ታይላንድ በዝናብ ወቅት በጎርፍ የሚጥለቀለቅ ሲሆን ይህም እስከ ጥቅምት ወር ድረስ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።