ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተሜ ደግነት በሀዋሳ
በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የታቦር መሰናዶ ትምህርት ቤት ከሰሞኑ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን የወሰዱ ተማሪዎች በጋራ ያደረጉት መልካም ተግባር የማህበራዊ ገጾች መነጋገሪያ ሆኗል።
ተማሪዎቹ የመጨረሻውን ፈተና በወሰዱበት ዕለት ለብሰውት የነበረውን የደንብ ልብስ በማውለቅ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን አቅም የሌላቸው ተማሪዎች ይገለገሉበት ዘንድ ለትምህርት ቤቱ ለግሰዋል።
ከአስተባባሪ ተማሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ጽዮን መንገሻ ለቢቢሲ ስትናገር ''የተቸገረ ተማሪን በመርዳት የአዕምሮ እርዳታ እናገኛለን፤ ከእኛ ቀጥሎ የሚመጡ ተማሪዎች እኛ የለበስነውን ተጠቅመው ለተሻለ ደረጃ ይደርሳሉ ብለንም እናስባለን'' ብላለች።
''ይሄ ሀሳብ ለትምህርት ቤቱ አዲስ አይደለም። ላለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ተመሳሳይ ተግባር ሲከናወን ቆይቷል'' ሲሉ የሚያስታውሱት የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ-መምህርት ትዕግስት ተረፈ በበኩላቸው ከአልባሳት በተጨማሪ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲማሩባቸው የነበሩ ንድፍ መሳሪያዎቻቸውን እንደለገሱ ነግረውናል።
ትምህርት ቤቱ በበጎ አድራጎት ክበቦቹ ስር አቅም የሌላቸው ተማሪዎችን ለመመገብ፣ የተወሰኑትን ደግሞ መጠለያ በኪራይ እንዲያገኙ ሲረዳ እንደቆየም ጠቅሰዋል።
የተማሪዎቹን በጎ አድራጎት የሚያሳየው ምስል በፌስቡክ ላይ ከተለጠፈ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ተቀባብለውታል።
ምስሉ ልባቸውን የነካቸው የሚመስሉ አስተያየት ሰጪ ተማሪዎቹን የሚያበረታታ ምላሻቸውን ችረዋል።
ባገኙት ምላሽ መደሰታቸውን የሚናገሩት መምህርት ትዕግስት ጉዳዩ በማህበራዊ ገፆች ላይ መነጋገሪያ መሆኑ በሌሎች ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ተመሳሳይ የመረዳዳት መንፈስ እንዲሰርፅባቸው ያነሳሳል ብለው እንደሚያምኑ አብራርተዋል።
በእዚህ በጎ ተግባር ተሳታፊ የሆኑ ተማሪዎች ቁጥር ወደ አንድ ሺ እንደሚጠጋ ርዕሰ-መምህርቷ ተናግረዋል።