ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርጀንቲና ከእስራኤል ጋር አልጫወትም አለች
ታትሟል
ለዓለም ዋንጫ መዳረሻ የወዳጅነት ጨዋታ ከእስራኤል ጋር ለማድረግ ቀን ቆርጣ የነበረችው አርጀንቲና ባለቀ ሰዓት "ይቅርብኝ" ብላለች።
እስራኤል በጋዛ ፍልስጤሞች ላይ እየፈጸመች ካለችው ጥቃት እንደምክንያትነት ተጠቅሷል።
የአርጀንቲናው አጥቂ ጉንዛሎ ሂግዌይን ለኢኤስፒኤን ስፖርት ጣቢያ ጨዋታው መሰረዙን አረጋግጧል፤ "በመጨረሻም ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ደርሰናል" ብሏል።
በአርጀንቲና የእስራኤም ኤምባሲም በይፋ የትዊተር ገጹ በእርግጥም የወዳጅነት ጨዋታው መሠረዙን አረጋግጧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ለአርጀንቲናው አቻቸው ጨዋታው እንዳይሰረዝ በስልክ ተማጽነዋቸው ነበር የሚሉ ዘገባዎች ቀደም ብለው ወጥተው ነበር።
የጨዋታው መሠረዝ በጥቂት ቀናት 120 ፍልስጤማዊያን በተገደሉበት ጋዛ መልካም ስሜትን ፈጥሯል።
በራማላህ መቀመጫውን ያደረገው የፍልስጤም እግር ኳስ ማኅበር ሌዮኔል ሜሲንና ጓደኞቹን የሚያመሰግን የምስጋና ደብዳቤ አውጥቷል።
"እሴት፣ ሞራልና ስፖርት ድል አድርገዋል። እነሆ ለእስራኤል ቀይ ካርድ ተሰጥቷታል" ሲሉ የማኀበሩ ሊቀመንበር ጂብሪል ራጀብ ለሬውተርስ ተናግረዋል።