ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰሜን ኮሪያ ቁልፍ ባለስልጣንና ፓምፒዮ በኒውዮርክ ተገናኙ
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ቀኝ እጅ የሆኑት ሰውና የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ማይክ ፖምፒዮን ስለ መጪው ጉባኤ ለማነጋገር በኒው ዮርክ ተገናኝተዋል።
ጌን ኪም ዮንግ ቾል ከቻይና መጥተው ከፖምፒዮ ጋር እራት አብረው ከተቋደሱ በኋላ በድጋሜ ሐሙስ እለት ለመገናኘት ቀን ቆርጠዋል።
ግለሰቡ ከሐያ ዓመታት ወዲህ በሰሜን ኮሪያ ከሚገኙ ከፍተኛ ሹማምንት መካከል አሜሪካን ሲጎበኙ የመጀመሪያው ሰው ናቸው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሰኔ 12 ተይዞ የነበረውን ጉባኤ የሰረዙ ቢሆንም አሁን ግን ሁለቱም ወገኖች ጉባኤው በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ እንዲካሄድ እንደ አዲስ ጥረት እያደረጉ ነው።
በሲንጋፖር ሊካሄድ ቀን የተቆረጠለት የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ጉባኤ እውን ከሆነ በስልጣን ላይ እያሉ የተገናኙ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በመሆን ታሪካዊ ይሆናል።
ረብዑ ምሽት ፖምፒዮና ጌን ኪም ለየብቻቸው ሆነው ለተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ህንፃ ተገናኝተዋል።
በኋላ ላይም ፖምፒዮ በቲውተር ገፃቸው ላይ "ዛሬ በኒው ዮርክ ከኪም ዮንግ ቾል ጋር ጥሩ እራት እየበላን ስለስራ ተነጋገርን ስቴክ ኮርን እና ቺዝ በምግብ ዝርዝሩ ላይ ነበር " በማለት አስፍረዋል።
ፖምፒዮ ከስብሰባው አስቀድመው የአሜሪካን አቋም ያስታውቃሉ።
ሰሜን ኮሪያ የትራምፕ አስተዳደር ኒውክለሮቿን የማውደም ተግባር ከሊቢያ ጋር ማነፃፀራቸውን በፅኑ ተቃውማ ነበር።
በሁለቱ ባለስልጣናት መካከል ተጨማሪ ውይይቶች ለሐሙስ ተቀጥረዋል።
የሰሜን ኮሪያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ቾ ሶን ሁኢ፣ የቀድሞው በደቡብ ኮሪያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩትን ሱንግ ኪምን በሁለቱ ኮሪያዎች ድንበር አካባቢ ማግኘታቸውን ቀጥለዋል።
እነዚህ ውይይቶች ተቋርጠው የነበረ ቢሆንም ከእሁድ ጀምሮ ግን ዳግም ቀጥለዋል።
በሲንጋፖርም ቢሆን የአሜሪካ የልዑካን ቡድን በሰሜን ኮሪያ አመራር ውስጥ ከጀርባ ሆነው በርካታ ጉዳዮችን ይሰራሉ ተብሎ የሚታመኑትን የፕሬዝዳንቱን ልዩ ረዳት ስለ ሎጀስቲክ እያነጋገሯቸው ይገኛል።
የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በበኩላቸው ከስብሰባው በፊት የሰሜን ኮሪያ አቋም ለማወቅ በሚል ፒዮንግ ያንግ ገብተዋል።
ሰርጌይ ላቭሮቭና ፖምፒዮ ለመጀመሪያ ጊዜ ረብዑ እለት በስልክ ተነጋግረዋል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ጉባኤ በታሰበለት ቀን ይካሄዳል ስትል ማረጋገጫ ሰጥታለች።