"ሙዚቃን የተማርኩት ከዩቲዩብ ነው፤ አሁን ታዋቂ ዘፋኝ ነኝ"

ታትሟል

ፍራንኪ ማክ በአንድ የጉዞ ድርጅት ውስጥ በወኪልነት በሚሰራበት ወቅት ነበር አንድ ሚስቱን በሞት የተነጠቀ ግለሰብ የባለቤቱን ተወዳጅ ሙዚቃ መድረክ ላይ ወጥቶ እንዲጫወትለት የጠየቀው።

ሙሉ ከሰዓቱን ሲለማመድና ሙዚቃውን ሲያጠና ቆየ። ሙዚቃውን የሚያቀርበው ምሽት ላይ ስለነበር በደንብ የመዘጋጀት ዕድልን ሰጠው።

''በጣም መጥፎ የሚባል ነበር አዘፋፈኔ። መጀመሪያ ላይ በድምጼ በጣም አፍሬ ነበር'' ይላል ፍራንኪ ሙዚቃ የጀመረበትን ጊዜ ሲያስታውስ። ነገር ግን እሱ በሙዚቃው ደስተኛ ባይሆንም እንኳን መድረክ ላይ ወጥቶ ሙዚቃውን እንዲጫወት የጠየቀው ግለሰብና ሌሎች ታዳሚዎች ጥሩ ምላሽ ነበር የሰጡት።

ዩቲዩብ በተሰኘው ማኅበራዊ መድረክ በኩል ሙዚቃን መማር እንደሚችል ሲረዳ ደግሞ፣ ጊዜ ሰጥቶ ሙዚቃን በነጻ መማር ጀመረ። አሁን ላይ በየመድረኩ እየዞረ ሙዚቃ በማቅረብ ሕይወቱን ይመራል።

የ28 ዓመቱ ፍራንኪ ማክ ሙዚቃ ለመጫወት ምን አይነት የአተነፋፈስ መንገድ መጠቀም እንዳለበት፣ እንዲሁም የድምጽ አወጣጥ መሠረታዊ ሕጎችን ከዩቲዩብ ነው የተማረው። ልምምዱንም በወዳጅ ዘመዶቹ ላይ ያደርግ ነበር።

ፍራንኪ ከዩትዩብ በተማረው ሙዚቃ አማካይነት አሁን ላይ ፕሮፌሽናል ዘፋኝ ሲሆን በርካታ አድናቂዎችም አሉት።

"በየሳምንቱ አንድ ሙዚቃ አጠናለሁ። ለእያንዳንዱ ሙዚቃ 45 ደቂቃ መድቤ እለማመዳለው።"

የ22 ዓመት ወጣት ሳለ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በመመለስ በአንድ ግዙፍ የግል መርከብ ውስጥ በዘፋኝነት ለመቀጠር አመለከተ። ነገር ግን ሥራውን ለማግኘት ካመለከቱት 13 ተወዳዳሪዎች መካከል ፍራንኪ ብቻ ተሰናበተ። ቀሪዎቹ ግዙፉ መርከብ ላይ እጅግ የናጠጡ ሀብታሞችን የማዝናናት ዕድል አገኙ። ፍራንኪ ግን እድሌ አመለጠኝ ብሎ እጅ እግሩን አጣጥፎ አልተቀመጠም።

ወዲያው ወደ ስኮትላንዷ ዋና ከተማ ኤደንብራ ተመለሰ። እዚያ ሄዶም ከአንዲት አነስተኛ መጠጥ ቤት ባለቤት ጋር ተዋወቀ። በግዙፉ መርከብ ላይ ስላመለጠውም ሥራም ነገራት።

"ተስፋ እንዳልቆርጥ ነገረችኝ። የራሴን መሳሪያዎች መግዛትና ሌሎች አማራጮችን መሞከር እንደምችል ነገረችኝ። እንዲያውም በየሳምንቱ አርብ አርብ እሷ መጠጥ ቤት ውስጥ መዝፈን እንደምችል ነገረችኝ።"

ፍራንኪ ጊዜ ሳያጠፋ ስፒከርና ማይክራፎን በመግዛት አርብ አርብ መዝፈን ጀመረ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ በአቅራቢያው በሚገኙ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከላት ውስጥ ሙዚቃውን ማቅረብም ጀመረ።

"በጣም ደስ አለኝ። የአረጋውያን መንከባከቢያ ውስጥ መዝፈን ስጀምር ደስተኛ ሆንኩኝ። አዳዲስ ሰዎችንም መተዋወቅ አስደሳች ነገር ነው" ይላል።

ፍራንኪ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ወደ ስፔን ሄዶ የሙዚቃ ሕይወቱን ለማስቀጠል ወሰነ። በአውሮፓውያኑ 2019 ላይ ደግሞ የቴንሪፌ ደሴት የመዝናኛ ሽልማት ላይ ተወዳድሮ በምርጥ አዲስ መጪ ዘርፍ አሸናፊ መሆን ችሏል።

"በካናሪ ደሴቶች አካባቢ ያሉ ዘፋኞች በሙሉ በውድድሩ ላይ ተሳትፈው የነበረ ሲሆን በጀማሪ ዘርፍ ማሸነፌ ደግሞ ትልቅ ስኬት ነው። በተለይ ደግሞ ዩቲዩብን ብቻ በመጠቀም በአጭር ጊዜ እራሴን ሙዚቃ አስተምሬ በዚህ ዘርፍ ማሸነፍ መቻል ለእኔ በጣም አስገራሚ ነው" ይላል።

ፍራንኪ 2019 ላይ በአዲስ ጀማሪ ዘርፍ ማሸነፉን ተከትሎ በማኅበራዊ መድረኮች በኩል የሚከተሉት አድናቂዎቹ ቁጥር በእጅጉ ጨመረ። ይህንን ያስተዋለው ፍራንኪ ጉዞውን ወደ አሜሪካ ለማድረግ ወሰነ።

ወደ አሜሪካ በመሄድም 2020 ላይ ላስ ቬጋስ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀው 'ሪል አዋርድስ' ላይ በመሳተፍ አሁንም በአዲስ ተስፈኛ ዘርፍ አሸናፊ መሆን ቻለ።

ለሦስት ቀናት በተካሄደው በዚህ ውድድር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙዚቀኞች የተሳተፉ ሲሆን ፍራንኪ ስድስት ሙዚቃዎቹን ለውድድሩ አቅርቧል።

"ልክ በውድድሩ ሳሸንፍ የነብስ ጥሪዬ መድረክ ላይ እንደሆነ ተረዳሁ" ይላል። "አድማጮች በሙዚቃዬ በጣም ሲዝናኑ አስተዋልኩኝ። ወደዚች ምድር የመጣሁት ሰዎችን ለማስደሰት እንደሆነ አመንኩኝ።"

አሁን ላይ ፍራንኪ ለ15 ቀናት የሚቆይ የሙዚቃ ድግስ ለማዘጋጀት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተመልሷል። በመቀጠል ደግሞ ለሦስት ዓመታት ወደ ሰራባት ሰፔን ይመለሳል።

ከዚህ በተጨማሪ ፍራንኪ ከ20 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገጹ በኩል በቀጥታ ሙዚቃውን ይጫወታል። ይህም ትልቅ ተቀባይነትና ተወዳጅነትን እንዲያገኝ አስችሎታል።

"በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ ጎዳናዎች ላይ ስንቀሳቀስ በሚያስገርም መልኩ በርካታ ሰዎች ያውቁኛል። በጣም ደስ የሚልና ልብን የሚያሞቅ ስሜት ነው" ይላል።

አክሎም "ምንም የማታውቃቸው ሰዎች ወደ አንተ ቀርበው ልክ እንደ ሚያውቁህ ሰው ሲያነጋግሩህ ትንሽ ግራ ያጋባል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ማንም የማያውቀኝ ወጣት ነበርኩኝ። አሁን ሌላ አይነት ሕይወት እየመራሁ ነው።"

ፍራንኪ ከታዋቂው ሙዚቀኛ ማይክል ቡብሌ ጋር በጥምረት የሰራው ሙዚቃ በሌሎች ማኅበራዊ መድረኮች በኩል እስካሁን 87 ሺህ ተመልካቾችን መሳብ ችሏል። በዩቲዩብ ደግሞ ሙዚቃው 1.4 ሚሊየን ተመልካቾችን አዝናንቷል።

"በጣም ደስተኛ ነኝ። አንድ ቀን ሆቴል ውስጥ ነበር የተገናኘው። በዚያው አብሮኝ ሙዚቃ ለመስራት ተስማማ። ምናልባት ይህንን አጋጣሚ ጭንቅላቴ ውስጥ 10 ሺ ጊዜ አስቤዋለው።"

"ከእሱ ጋር አብሬ ልዘፍን እንደሆነ ስነግራቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች መልሳቸው ሳቅ ነበር። የምርም አብሬው ሙዚቃውን ስሰራ እኔ እራሱ አላመንኩትም ነበር" ይላል ፍራንኪ።

ፍራንኪ አሁን ላይ በርካታ አድናቂዎችና ተከታዮችን ማፍራት ችሏል። እንደ ቀልድ ዩቲዩብን ብቻ በመጠቀም ያሳደገው የሙዚቃ ክህሎቱ እንደ ማይክል ቡብሌ ካለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ማትረፍ ከቻለ ሙዚቀኛ ጋር እስከ መስራት አድርሶታል።