በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሚሳተፉ ቡድኖች ከ32 ወደ 36 ያድጋል ተባለ

ታትሟል

በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2024/25 የውድድር ዓመት ጀምሮ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ከ34 ወደ 36 ከፍ እንደሚል የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አስታወቀ።

በአዲሱ ሕግ መሰረት ተሳታፊ ቡድኖቹ በ10 የውድድር ሳምንታት ውስጥ ስምንት ጊዜ የሚጫወቱ ይሆናል።

ነገር ግን ከየሊጉ ሁለት ተጨማሪ ቡድኖችን በውድድሩ ባላቸው ታሪክ አወዳድሮ ለማስገባት ታስቦ የነበረው እቅድ ተግባራዊ አይሆንም ተብሏል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሴፍሪን ስለ አዲሱ ሕግ ሲናገሩ ''ሁሉም ክለቦች የመሳተፍ ህልማቸውን ማሳካት ይችላሉ'' ብለዋል።

በዚህም ቡድኖች ከዚህ በፊት ለዓመታት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ያላቸውን ታሪክ ከግምት ውስጥ ከማስገባት ይልቅ በየሊጋቸው ያላቸው ነጥብ እንዲሁም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሚኖራቸው ተሳትፎ እንደሚያስመርጣቸው ተገልጿል።

ለምሳሌ ከ2024/25 ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው አዲሱ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እና የሆላንድ ኤርዲቪሲ ተጨማሪ ሁለት ክለቦችን ማሳተፍ ይችላሉ።

ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ከሳምንታት በኋላ በሚጠናቀቀው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ብዙ ክለቦችን ያሳተፉትና ውጤታማ ሆነው መጓዝ የቻሉት ከእንግሊዝ እንዲሁም ከሆላንድ ሊግ የመጡ ክለቦች በመሆናቸው ነው። ስለዚህ አምስተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁት ክለቦች በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የመሳተፍ እድል ይሰጣቸዋል ማለት ነው።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እንደሚለው አምስተኛ ሆነው ጨርሰው በቀጥታ ከሚያልፉት ሁለት ቡድኖች በተጨማሪ ቀሪዎቹ ሁለት ቡድኖች ደግሞ በውድድር ዓመቱ በሁሉም የአውሮፓ ሊጎች አምስተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁት ተወዳድረው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግን እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ አሰራር ይዘረጋል።

ማሕበሩ መጀመሪያ ላይ አቅርቦት የነበረውን ቡድኖች ባላቸው ታሪክ ላይ የመመስረት ሀሳብ ትልልቅ ክለቦችን ብቻ ለማካተት የተደረገ ነው በሚል የቀረበበትን ከፍተኛ ተቃውሞና ትችት ተከትሎ ነው ሃሳቡ ውድቅ የሆነው።

ይህ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆን ቢሆን ኖሮ በአውሮፓ መድረክ ለዓመታት ጎልተው መታየት የቻሉ ትልቅ ክለቦች በሊጋቸው ደካማ አቋም ቢያሳዩ እንኳን በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የመሳተፍ ዕድል ያስገኝላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በምድብ ድልድሉ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ከ6 ወደ 10 ከፍ እንዲል መደረጉን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አስታውቋል። ምንም እንኳን እንደ ሊቨርፑል ያሉ ክለቦች የጨዋታዎች መደራረብ ተጫዋቾችን ለጉዳት እያጋለጠ ነው የሚል ቅሬታ ቢያሰሙም ማህበሩ ግን እንደውም የጨዋታዎችን ቁጥር እንደሚጨምር ገልጿል።

አዲስ የቀረበው ሕግ በሁሉም በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ስራ አስፈጻሚ አባላት፣ የየአገራቱ ሊጎች እንዲሁም ብሄራዊ የእግር ኳስ ማህበራት በሙሉ ድምጽ ድጋፍ ማግኘቱን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በቀድሞው ሕግ መሰረት ቡድኖች በስምነት ምድቦች ተደልድለው ከየምድቦቹ ከፍተኛ ነጥብ ያላቸው ሁለት ቡዶኖች ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፉ ነበር የሚደረገው። በአዲሱ ሕግ መሰረት ግን ይህ ይቀራል ተብሏል።

በአዲሱ አሰራር ቡድኖች በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ተዘጋጅቶላቸው የሚወዳደሩ ይሆናል። ቡድኖቹ ስምንት ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ሲሆን አራት በሜዳቸው አራት ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ ማለት ነው። በመጀመሪያው ዙር ከአንድ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፋሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ከዘጠነኛ እስከ 24ኛ ቦታ ይዘው የሚያጠናቅቁት ቡድኖች ደግሞ በደርሶ መልስ ተጫውተው አሸናፊዎቹ 8 ቡድኖች ደግሞ ቀጣዩን ዙር ይቀላቀላሉ።