ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ 'ሊሰልለኝ ይችላል' ያለችውን የቻይና ቴሌኮም ኩባንያ አገደች
አሜሪካ የቻይናው የቴሌኮም ተቋም ዩኒኮም በግዛቷ እንዳይሠራ አገደች።
የዩኒኮም እንቅስቃሴ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት እንደሆነና ተቋሙ አሜሪካን ሊሰልል እንደሚችልም ተገልጿል። እነዚህን ምክንያቶች በማጣቀስ የአሜሪካ ብሔራዊ የኮምዩኒኬሽን ኮሚሽን የዩኒኮምን ፈቃድ ነጥቋል።
ዩኒኮም በ60 ቀናት ውስጥ አሜሪካ ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲያቋርጥም ትዕዛዝ ተላልፏል።
አሜሪካ የቻይና የቴሌኮም ድርጅትን ፈቃድ ስትነጥቅ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ጥቅምት ላይ የቻይና ቴልኮም ፈቃድ ተሰርዟል።
የኮምዩኒኬሽን ኮሚሽን ኃላፊ ጀሲካ ሮዝንወስል እንዳሉት፤ በቻይና መንግሥት የሚተዳደሩ የቴሌኮም ድርጅቶች ለስልክ መስመሮች ደኅንነት አስጊ የሆነ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ አሳማኝ ማስረጃ አግኝተዋል።
የቻይና የቴሌኮም ተቋሞች አስጊ እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።
ዩኒኮም ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ "የአሜሪካው ቅርንጫፋችን የአሜሪካንን ሕጎች እና ደንቦች ተከትሎ ሲሠራ ቆይቷል። ባለፉት 20 ዓመታት ደንበኞቻችን የሚተማመኑበት አገልግሎት ሰጥተናል" ብሏል።
በአሜሪካ የተላለፈውን ውሳኔ በቅርበት እንደሚከታተሉትም አክለዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣኖች ባለፉት ዓመታት የቻይና የቴክኖሎጂ ተቋሞች ላይ እርምጃ መውሰድ ቀጥለዋል።
ለአሜሪካ ደኅንነት ስጋት የሆኑ ድርጅቶች ፈቃዳቸው እንዲነጠቅ የሚፈቅድ አሠራር ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አጽድቀዋል።
ሁዋዌ፣ ዜድቲኢ እንዲሁም ሌሎች ሦስት የቻይና የቴሌኮም ኩባንያዎች በአሜሪካ እግድ ተጥሎባቸዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በጥቅምት ወር ለደኅንነትና ለውጭ ጉዳይ ስጋት ናቸው ያላቸውን የቻይና ተቋማት ማገዱ አይዘነጋም።
በእነዚህ ተቋማት አማካይነት የሚሰበሰቡ መረጃዎች ለቻይና ወታደራዊ ኃይል ግንባታ እየዋሉ ነው የሚል ክስ ከአሜሪካ ተሰንዝሯል።
የቻይና መንግሥት ለቴሌኮም ተቋሞቹ "መረጃ የመሰብሰብ፣ የማከማቸት፣ የማሰናከልና ወደሌላ አቅጣጫ የማስተላለፍ ፈቃድ ሰጥቷል" ብላለች አሜሪካ።
ይህም አሜሪካን ለመሰለልና በሌላም መንገድ አሜሪካን ለመጉዳት ያለመ እንደሆነ አሜሪካ ይፋ አድርጋለች።