በዲሞክራቲክ ኮንጎ ማረሚያ ቤት በተፈጠረ ሁከት በጅምላ የደፈሩ ታሳሪዎች ጥፋተኛ ሆነው ተገኙ

ታትሟል

በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ማረሚያ ቤት ውስጥ የተፈጠረ ሁከትና ብጥብጥን ተከትሎ በርካታ ሴት እስረኞች የተደፈሩ ሲሆን አስር ወንድ እስረኞችም ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

በከፍተኛ ሁኔታ የተጨናነቀ ነው በተባለው ማረሚያ ቤት ለሶስት ቀናት በዘለቀ ሁከትና ብጥብጥም ነው ሴቶቹ እና ታዳጊዎቹ የተደፈሩት።

ካሳፓ ማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ 37 ሴቶች እና ታዳጊዎች ለሶስት ቀናት ያህል በተደጋጋሚ መደፈራቸውንም መስክረዋል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ዓመት በተፈጠረው ረብሻ ከተደፈሩ ሴቶች መካከል እርግዝናን ጨምሮ ኤችአይቪም በደማቸው እንደተገኘም ተገልጿል።

10 ታራሚዎች የገንዘብ መቀጮ እና 15 ተጨማሪ አመታትም በእስር እንዲቀጡ ተወስኗል።

ምንም እንኳን አንዳንድ ሴት እስረኞች ማስረጃ ለመስጠት በጣም ፈርተው የነበረ ቢሆንም በርካቶች ግን በረብሻው ወቅት መደፈራቸውን ለወታደራዊ አቃቤ ህግ መስክረዋል።

"ፍትህ ለማግኘት ረጅም ትግል ካደረግን በኋላ ይህ ብያኔ በመወሰኑ ተደስተናል" በማለት የተጎጂዎቹ ጠበቃ ሜላኒ ሙምባ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 2020 የተነሳውን ሁከት ተከትሎ ወንድ እስረኞች ለቀናት ያህል ይህንን ማረሚያ ቤት ተቆጣጥረውት ነበር።

ወንድ ታራሚዎቹ በእስር ቤቱ ላይ እሳት የለቀቁበት ሲሆን በተጨማሪ የ16 አመት ታዳጊን ጨምሮ በርካታ ሴቶች ላይ በተደጋጋሚ ወሲባዊ ጥቃት አድርሰውባቸዋል።

የጸጥታ ሃይሎች የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ስር ከማዋላቸው በፊት 20 የሚሆኑ እስረኞች እና የእስር ቤቱ ጠባቂ ተገድለዋል ተብሏል።

በጅምላ የተደፈሩትን ሴቶችና ታዳጊዎችን አስመልክቶም ሂውማን ራይትስ ዋች አንድ ሪፖርት አውጥቶ የነበረ ሲሆን ባለስልጣናቱ ጥቃቱን እንዲመረምሩ እና ለተጎዱትም ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ተቋም እንዳስታወቀው 800 እስረኞችን ለመያዝ በተገነባው ማረሚያ ቤት ሁከቱ በተፈጠረበት ወቅት በተጨናነቀ ሁኔታ 2 ሺህ እስረኞች ታስረውበት ነበር።

በማረሚያ ቤቱ የንፅህና ጉድለት፣ ደካማ የጤና አጠባበቅና ሌሎች ችግሮች እንዳሉ በመጥቀስ ረብሻ ሊፈጠር እንደሚችል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጥም ባለስልጣናቱ ችላ እንዳሉትም ተቋም በሪፖርቱ አስፍሯል።

በኮንጎ የሂውማን ራይትስ ዋች ከፍተኛ ተመራማሪ ቶማስ ፌሲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአስሩ ታራሚዎች ክስ "እንደ መጀመሪያ እርምጃ መታየት ያለበት" ብለዋል።

"በግርግሩ ወቅት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ከነበሩት 56 ሴት እስረኞች መካከል 37ቱ ሴቶች እና አንዲት ታዳጊ ሴት በወንድ እስረኞች ተደፍረናል ብለው ለሉቡምባሺ አቃቤ ህግ መስክረዋል። እናም እያንዳንዱ ወንጀል የፈፀመ ሁሉ በወንጀል ሊጠየቅ ይገባል" ሲሉ ቶማስ ፌሲ በኢሜይል በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል

ተመራማሪው በተጨማሪም የኮንጎ ባለስልጣናት እስረኞችን "መጠበቅ ተስኗቸዋል፤ ለታራሚዎች ደህንነት መስጠት አልቻለም" ብለዋል።

የተከሳሾቹ ጠበቃ ኖኤላ ባሺዚ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ረቡዕ በተሰጠው ቅጣት ላይ ይግባኝ ለማለት ደንበኞቿቻቸውን እንደሚያማክሩ ተናግረዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች በባለፈው አመት ባወጣው ሪፖርት የ16 አመት ታዳጊን ጨምሮ፣ ቢያንስ ሰባት እስረኞች በረብሻው በተፈጠረው መደፈር አርግዘዋል። የተጎጂዎችን ጠበቆች ዋቢ ያደረገው ኤኤፍፒ በበኩሉ ያረገዙ ሴቶችን 16 አድርሶታል።