የበርሊን ማራቶን አሸናፊዋ ጎተይቶም ዕቅዴን አሳክቻለሁ አለች

ታትሟል

በማራቶን ውድድር ለመጀረሚያ ጊዜ ተወዳድራ የ2021 የበርሊን ማራቶን ያሸነፈችው አትሌት ጎተይቶም ገብረ ስላሴ በውድድር መድረኩ ያሰብኩትን አሳክቻለሁ አለች።

አትሌት ጎተይቶም ጀርመን በርሊን ላይ በተካሄደው የማራቶን ውድድር የጠበቀችውን ሰዓት ማሳካት መቻሏንም ተናግራለች።

"የመጀመሪዬ ስለሆነም 2፡20 እሮጣለሁ ብዬ ነው የመጣሁት። ያሰብኩትን ነው የሮጥኩት" ብላለች።

ጎተይቶም በውድድሩ በ2፡20፡09 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ ነው አሸናፊ በመሆን ያጠናቀቀችው።

ትናንት በተካሄደው የበርሊን ማራቶን በተለይ በወንዶች የማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰን ሳይሻሻል የቀረው በበርሊን የነበረው የአየር ሁኔታ ሞቃታማ መሆኑ በአትሌቶች እንደምክንያት ተነስቷል።

አትሌት ጎተይቶም ግን ይህ የማራቶን ውድድሯ የመጀሪያዋ መሆኑን በማስታወስ፤ "የመጀመሪያዬ እንደመሆኑ ማራቶን ውስጡ ምን እንደሆነ እራሱ አላወኩም ነበረ። . . . ከ35ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ድካምም ስለነበር የዛኔ ነው ሙቀት እንደነበር የታወቀኝ" ብላለች።

የበርሊን ማራቶን አሸናፊዋ ጎተይቶም ገብረ ስላሴ ከትናንት ውድድሯ የማራቶን ውድድር ልምድ ማግኘቷን በመጥቀስ ወደፊት ከ02፡20፡00 በታች ለመሮጥ እቅዷ እንደሆነ ተናግራለች።