ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ 2013፡ ቦርዱ ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አያሟላም ላሉት ሴናተሮች ምላሽ ሰጠ
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኢትዮጵያ ከሳምንታት በኋላ የምታካሂደው ምርጫ 'አሁን ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም' ላሉት የአሜሪካ ሴናተሮች ምላሽ ሰጠ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለሴናተሮቹ በጻፉት ደብዳቤ ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲያብብና የሰብዓዊ መብት እንዲጎለብት ከምታደርገው ጥረት አንፃር በቅርቡ አምስቱ ሴናተሮች በሰጡት አስተያየት 'ተገርሜአለሁ' ብለዋል።
ከቀናት በፊት አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች በቀጣይ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ነጻ፣ ሚዛናዊ እና ግልጽ ሆኖ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አያሟላም ብለው ነበር። ሴናተሮቹ ይህን ያሉት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጆፍሪ ፌልትማን ወደ ቀጠናው ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት በጻፉላቸው ደብዳቤ ነበር።
ሰብሳቢዋ በበኩላቸው ዛሬ ይፋ በተደረገው ደብዳቤስድስት ዋና ዋና ነጥቦች አስፍረው ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርት አያሟላም ላሉት ሴናተሮች ምላሽ ሰጥተዋል። በተመሳሳይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ ቀጣዩን ምርጫ የሚያስፈጽመው ቦርድ ገለልተኛ መሆኑን በመጥቀስ ለሴናተሮቹ አስተያየት ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም።
ብርቱካን በደብዳቤያቸው ምን አሉ?
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ተቋም እንደመሆኑ፤ ቀጣዩ ምርጫ ዓለም አቀፍ ሕግጋት የተከተለ እንዲሆን እየጣረ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ የሕዝብ ብዛትን፣ ያላደገ የዲሞክራሲ ባሕል፣ በየጊዜው እየተስፋፋ የመጣውን የደህንነት ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀጣዩ ምርጫ እንከኖች እንደሚኖሩት ይጠበቃል ብለዋል።
ነገር ግን እነዚህ ጉዳዮች መራጩ ድምፁን ሲሰጥ እንቅፋት እንዳይሆኑ ለማድረግ የአጭር ጊዜ መፍትሄዎች ተቀምጠዋል። ቢሆንም በምርጫው የሚሳተፉ ሁሉ ስለሂደቱ ሲያስቡ እኚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው ብለዋል።
ሰብሳቢዋ አክለው የምርጫው ተሳታፊዎች በቅድመ ምርጫ ሂደቱ በነቂስ ተሳትፈዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በቦርዱ ከተመዘገቡ 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች 46ቱ ዕጩዎቻቸውን አሳውቀዋል። 9 ሺህ ዕጩዎች በፌዴራልና በክልል ደረጃ ይሳተፋሉ። ይህ ቁጥር በኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ እስከዛሬ ከተመዘገበው ትልቁ ነው ይላል የሰብሳቢዋ ደብዳቤ።
መግለጫው ጨምሮ ከ190 በላይ ሃገር በቀል የሲቪክ ሶሳይቲ ማሕበራት የምርጫ ትምህርት እንዲሰጡ ፈቃድ እንደተሰጣቸውና 34 ሃገር በቀል ድርጅቶች ደግሞ ምርጫውን እንዲታዘቡ ፈቃድ ማግኘታቸውን ጠቅሷል።
እነዚህ ምርጫ ታዛቢ ድርጅቶች ድምፅ አሰጣጡንና ሌሎች ሂደቶችን እንዲታዘቡ ከ100 ሺህ በላይ ባለሙያዎችን ያሰማራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሰብሳቢዋ መግለጫ ያትታል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች በምርጫ ሂደቱ ላይ በሃገሪቱ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች በሃገሪቱ እየተዘዋወሩ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው፤ እነዚህ ፓርቲዎች ፈተና እንደሚገጥማቸው የታመነ ቢሆንም ምርጫ ቦርዱ የሚቀርቡት ቅሬታዎች ለመፍታት እየጣረ ነው ብለዋል ሰብሳቢዋ።
ቅሬታዎች በተቋሙ አቅም የሚፈቱ ሲሆኑ ቦርዱ የታሰሩ ዕጩዎችንና የፓርቲ መሪዎችን እስከማስፈታት ድረስ ጥረት ያደርጋል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጣቸው የሚድያ ጊዜም በሁሉም ፓርቲዎች ዘንድ በፍትሃዊነት እንዲከፋፈል መደረጉን አሳውቀዋል።
ሰብሳቢዋ በቦርዱ ማሕበራዊ ድር አምባ ገፆች ባሰራጩት መግለጫ ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ብዙ ጥረት መድረጉን አንስተዋል።
ከእነዚህ ጥረቶች መካከል የምርጫው ተሳታፊዎችን ሐሳብና አስተያየት በምርጫው መመሪዎች ውስጥ ማስገባት አንዱ ነው ብለዋል።
"በዚህም መሠረት እንደ የምርጫ ሳጥን፣ ስክሪኖች፣ ማሸጊያዎች እና የማይጠፋ ቀለም ያላቸው 'ማርከሮች' ግዢ፣ የምርጫ ወረቀት ዲዛይንና ሕትመት እንዲሳካ ተደርጓል። እነዚህ እርምጃዎችና ሌሎችም የዘንድሮውን ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በላቀ ተዓማኒ እንዲያደርገው ያግዛል" ብለዋል።
ሰብሳቢ የ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ አስተዳዳሪ በኢትዮጵያ ታሪክ ግልፁ ነው ብለዋል።
"ከፈረንጆቹ 2019 መገባደጃ ጀምሮ በምርጫው ከሚሳተፉ አካላት ጋር 50 የውይይት መድረኮች ተደርገዋል። ይህ የሆነው ቦርዱ ከፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቴሌግራምና ዩትዩብ ገፆቹ ከሚያደርገው መደበኛ ግንኙነት በተጨማሪ ነው።"
ጥልቅ ውይይቶች ያስፈለጉት ተሳታፊዎች ከምርጫው ሂደት ጋር ተያይዞ ያሉትን ፈተናዎች እንዲረዱትና መፍትሄ እንዲያዋጡ ለማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሃገር በቀልና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ክፍት ነው ያሉት ሰብሳቢዋ በኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢኒስቲትዩትና በናሽናል ዴሞክራቲክ ኢኒስቲትዩት ትብብር ለተቋቋመው ዓለም አቀፉ ምርጫ ታዛቢ ሚሽን ጥሪ አቅርበዋል።
"መሰል ልዑካን የምርጫውን ግለፅነት ከፍ ያደርጉታል" ብለዋል ሰብሳቢዋ።
ሰብሳቢዋ በምርጫ ወቅት የሚደረጉ ለውጦች ቴክኒካዊ፣ ፋይናንሳዊ፣ ፖለቲካዊና የደህንነት መዋቅር ስጋት ሊያመጡ ይችላሉ ብለዋል በመግለጫቸው።
"ለውጥ ሲካሄድ ወቅቱን መጠበቁን፣ ዋጋን፣ ጥልፍልፍነቱን እንዲሁም ግልፅነቱን ከግምት ያስገባ መሆን አለበት። ስለዚህ በዚህ ወቅት የሚደረጉ ወሳኝ ለውጦች አይበረታቱም። በምትኩ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫው ተሳታፊዎች ተግባራዊ ለሚሆኑ መመሪዎች ተገዢ እንዲሆኑና ቅሬታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲያቀርቡ ያበረታታል" ይላል መግለጫው።
ሰብሳቢዋ መግለጫቸውን ሲያጠቃልሉ አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዲሞክራሲ ለውጥ ሂደት በቅርበት መከታተሏንና መደገፏን እንደምትቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ፤ አዲስ አበባ ከሚገኙት የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር እንደምንገናኝ አስባለሁ ብለዋል።