ነገ-ዛሬ እያሉ ሥራን የመግፋት አባዜ ምንድን ነው? መፈወስ ይቻላል?

ታትሟል

ክብድ ከሚልዎ የሥራ ባልደረባዎ ኢሜይል ይደርስዎታል፡፡ መመለስ ግን ያቅቶታል፡፡ ለምን?

ምናልባት ምላሹ ‹አመሰግናለሁ› የሚል ቃል ብቻ ሊሆን ይችላል እኮ፡፡ ነገር ግን ምላሹን ለነገ ያሳድሩታል፡፡

የሆነችን አንድ ዓረፍተ ነገር አስተካክሎ የሚላክ ሰነድ ሊኖርዎ ይችላል፡፡ ሆኖም ያን አድርጎ መላክ አይሰምርልዎትም፡፡ "በኋላ" ይሉና ከድነው ያስቀምጡታል፡፡

ለአለቃዎ አሁኑኑ መደወል ይኖርብዎ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስልኩን ማንሳትና የአለቃዎን ቁጥር መምታት ክብድ ይልዎታል፡፡ ለምን እንደዚያ እንደሚሰማዎ ግን አያውቁም፡፡

"በቃ በኋላ ላይ እደውልላታለሁ" ይሉና ቀጠሮ ይይዛሉ፡፡ የማይሰምር ከራስ ጋር ቀጠሮ፡፡

ከትምህርት ቤት ይዘውት የመጡት ደቂቃ የማይወስድ የቤት ሥራ ይኖራል፡፡ ዛሬ ነገ እሠራዋለሁ እያሉ ውለው አድረዋል፡፡ ከርመዋል፡፡ ለምን?

ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉንም ተግባራት ለመፈጸም ለእያንዳንዳቸው 3-3 ደቂቃዎች በቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የሆነ ነገር ጨምድዶ ይይዝዎታል፡፡

እንዲህ ዓይነት ሰው ከሆኑ ሥራ መግፋት ወይም ሥራ ማሳደር አባዜ (procrastination) አለብዎ ማለት ነው፡፡

አንድ ራሱን የቻለ መለስተኛ የአእምሮ ግድፈት ነው፡፡ ሆኖም መጨነቅ አይኖርበዎትም፡፡ ይህ የእርስዎ ችግር ብቻ አይደለም፤ የሚሊዮኖች እንጂ፡፡

ተመራማሪዎች እንደሚሉት ጥቃቅን ተግባራት ወዲያውኑ ካልተፈጸሙ አእምሯችንን ይቆጣጠሩታል፡፡ አንድን ተግባር በተገቢው ጊዜ መፈጸም ግን እፎይታ ነው፡፡

በአገራችን ብሂል መሰረት ደግሞ 'የእህል ለነገ ያገለግላል የሥራ ለነገ ያጀለጅላል' ነው ነገሩ።

በሌላ አነጋገር ሥራን ማሳደር ሸክም ነው፡፡ የአእምሮ ሸክም፡፡ ኩንታል እህል ተሸክሞ የማደር ያህል አድካሚ ነው፡፡ ሆኖም አባዜው ቶሎ አይለቅም፡፡

ታዲያ ምን ተሻለ?

ወደ መፍትሄው ከመሄዳችን በፊት አእምሯችን ለምን እንዲያ እንደሚሰራራው ብንረዳ የተሻለ ነው፡፡

ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ ሥራን ማዋል ማሳደር የሚያበዙ ሰዎች ጥሩ እንቅልፍ የላቸውም፡፡ በሥራ ውጥረት ይንገላታሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና አለቆቻቸው ጋር የሻከረ ግንኙነት ነው የሚኖራቸው፡፡

የአእምሮ ጤና አዋቂዎች እንደሚሉት ሥራን ማዋል ማሳደር የሚያበዙ ሰዎች ሥራን በወቅቱና በጊዜው ከሚወጡ ሰዎች ይልቅ ለድብታና ለአላስፈላጊ ጭንቀት የተጋለጡ ናቸው፡፡

በሥራ ዓለም ብቻም ሳይሆን በፍቅር ግንኙነታቸውም እክል ይገጥማቸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው ለራሳቸው ያለመታመን ስሜት ስለሚያንገላታቸው ነው፡፡

ሰዎች ለምን ሥራን ማዋል ማሳደር ይፈልጋሉ ተብሎ በተደረገ ምርመራ አጥጋቢና ሁሉንም ያስማማ ምላሽ አልተገኘም፡፡

ሆኖም አንድ ሥራን ለመሥራት የሚያስፈልገን ጉልበትና ወኔ (ምንም እንኳ ሥራው ተራ ቢሆንም) ለጊዜው የአእምሮ ውጥረት እንዳይፈጥርብን ስንፈራ ሥራውን እንገፋዋለን፡፡

ሥራን አውለን ስናሳድር ከሥራ ሐሳቡ የተገላገልን ነው የሚመስለን፡፡ እውነታው ግን በተቃራኒው ነው፡፡

የሥራውን ጭንቀት ተሸክመን ነው የምንቆየው፡፡ በሌላ አነጋገር ሥራውን ስንገፋው ሥራው ሳይሆን እራሳችንን ነው ከእፎይታ የገፋነው፡፡ የአእምሯችን ጓዳ ሥራውን እንደተሸከመው ነው የሚንከላወሰው፡፡

ሀቁ ሥራውን ሠርቶ ከመገላገል በላይ እፎይታ የለም፡፡

ሥራን የሚያሳድሩ ሰዎች ብዙዎቹ ለሥራው ደንታ የሌላቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ አንድን ተግባር የራሱ ጉዳይ የሚሉ ሰዎች አይደሉም፡፡ እውነተኛው ስሜታቸው ቢፈተሸ ሰርተው ቢገላገሉ ይመርጣሉ፤ ወኔው ይከዳቸዋል እንጂ፡፡

ሥራውን በወቅቱ አለመስራታቸው ስለሚቆጠቁጣቸው አእምሯቸው አንዳች ነገር ያውከዋል፡፡ ምቾት ይነሳቸዋል፡፡

"ምንድነው ግን ችግሬ? ለምንድነው ሥራዬን በሰዓቱ የማልሰራው? በቃ ይቺን እንኳ የመሥራት ብርታት የሌለኝ ከንቱ ሆንኩ ማለት ነው?" እያሉ ይብሰለሰላሉ፡፡

በጊዜው ያልተሠሩ ተግባራት ምንም እንኳ ትንሽ ቢሆኑም አስጨናቂ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ለላከልን የጽሑፍ መልእክት "ደርሶኛል አመሰግናለሁ" ብሎ ለመጻፍ ሊከብደን ይችላል፡፡

አንድም ለዚያ ሰው ያለን ስሜት ከባድ ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡

ምላሽ መስጠቱ ተራ ተግባር ቢሆንም ተግባሩን በገፋነው ቁጥር ግን እየገዘፈ ሄዶ ተራራ ሊያክል ይችላል፡፡

እንዴት ችግሩን እንቅረፈው ታዲያ?

ፕሮፌሰር ቲሞቲ በኦታዋ ካርልተን ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው፡፡ ሥራን በማሳደር አባዜ ዙርያ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡

የመጀመርያው ምክራቸው አንድን ተግባር ወዲያውኑ መፈጸም የሚሰጠውን እርካታ ማሰብ መቅደም እንዳለበት ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ተግባሩን ማሳደር እንዴት ትክክል እንደሆነ ለሚሰብከን አእምሮ ተግባሩን አሁኑኑ መፈጸም እንዴት ግልግል እንደሆነ መንገር ያሻል ነው የሚሉት፡፡

ሌላኛው ተመራማሪና የማነቃቂያ ንግግር አዋቂ ዴቪድ አለንም በዚህ ይስማማሉ፡፡

"2 ደቂቃ ለማትወስድ ሥራ ሰው እንዴት 2 ሰዓት ይብሰለሰላል?" ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ምን ማለታቸው ነው፤ ተግባሩን ለመግፋት ስንል አእምሯችንን ለማሳመን/ለማታለል የምንጥረውን ሩብ ሰዓት ተግባሩን ለመፈጸም ብናውለው ሥራው አልቆ ይጠብቀናል፡፡

ሌላው ቀላል ሥራን ላለመግፋት መፍትሄ ሆኖ የተወሰደው ተግባራቱን ለመፈጸም የተመቸ ሰዓት መመደብ ነው፡፡ አንድን ቀላል ሥራ ከማሳደር ይልቅ ሌላ ሥራ እየሠራን ልናሳካው እንችላለን፡፡

ለምሳሌ ለጽሑፍ መልእክቶች ጠዋት ጠዋት ከሥራ ወደ ቤት ስንሄድ በታክሲ ውስጥ ሆነን ተግባሩን የመፈጸም ልማድን ልናዳብር እንችላለን፡፡

ኩሽና የተከማቹ ያልታጠቡ ሳህኖችን ለማጽዳት የጠዋት ክፍለ ጊዜን መርጠን የማለዳ ሙዚቃ ከፍተን ልንፈጽመው እንችላለን፡፡

ካልሲ ማጠብ ለብዙዎች የማይወጡት ተግባር ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ከማለት የምንወደውን የሬዲዮ ፕሮግራም ወይም የቋንቋ ትምህርት በጆሮ ማዳመጫ እየሰማን የካልሲ ማጠቡን ሥነ ሥርዓት አስደሳች ተግባር ሆኖ እንዲሰማን ልናደርገው እንችላለን፡፡

ይህ አግባብ የሆነ ሰዓትን ለጥቃቅን ነገር ግን አታካች ለሚመስሉ ሥራዎች መመደብ ተግባሩን አክብደን እንዳናየው ያግዘናል፡፡ ይህን ስንለማመድ ደግሞ አንድን ተራ የሚባል ሥራ መግፋት እናቆማለን፡፡

ሌላው የአእምሮ አዋቂዎች ምክር አንድን ሥራ በማሳደራችን ራሳችንን ደጋግመን አለመውቀስ ነው፡፡

ከዚህ ራስን የመውቀስ ስሜት ተመልሶ መጥፎ የስሜት አውድ ስለሚፈጥር ሥራውን ብቻም ሳይሆን እኛንም ይጎዳናልና፡፡

ካልሲ ማጠብ ስለሰነፍን ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ነን ማለት አይደለም፡፡ የስሜት ብርታት ብቻ ነው የጎደለን፡፡ ይህ ደግሞ ነገሩን ቀላል አድርጎ በማሰብ ብቻ ሊስተካከል የሚችል ነው፡፡