ሴቶችን አንቋሿል የተባለው የቻይና ድርጅት ወቀሳ ደረሰበት

ታትሟል

ታዋቂው የቻይና መጠጥ ሻጭ ድርጅት በምርቶቹ ላይ ሴቶችን የሚያንቋሽሹ መልዕክቶች አስተላልፏል ተብሎ ወቀሳ ገጠመው።

ድርጅቱ በበይነ መረብ የገጠመውን ትችት ተከትሎ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

ሴክሲ ቲ የተሰኘው ተቋም ሴቶችን ምርቶቹን እንድ 'ማሻሻጫ' ተጠቀተሞባቸዋል፤ አልፎም ደንበኞች ትኩስ መጠጡን እየጠበቁ ሴቶችን ማግኘት ይችላሉ በማለቱ ነው የተወቀሰው።

ድርጅቱ ከዚህ በፊትም "ጌታዬ እፈልግዎታለሁ" የሚል መልዕክት ያለበት የሻይ ቅጠል ሸጧል ተብሎ ተወቅሶ ነበር።

ኩባንያው ከወቀሳው በኋላ "ሴቶችን የማንቋሸሽ" ምንም ዓላማ እንደሌለው አሳውቆ ነበር።

መጠጥ ሻጩ ድርጅት ሴቶችን የሚያንቋሽሹ ናቸው የተባሉትን የሻይ ኩባያዎች ከገበያ ውጭ እንደሚያደርግ እና "በድርጊቱ እጅግ እንዳፈረ" ገልጿል።

ሴክሲ ቲ በቅርቡ 'ቻንግሻ' በተባለው ዘይቤ መልዕክት የተፃፈባቸው በርካታ ኩባያዎች ለገበያ አቅርቦ ነበር።

ቋንቋው በሁናን ግዛት በስፋት የሚነገር ሲሆን ድርጅቱ በዚህ ግዛት 270 ያክል ሱቆች አሉት።

ኩባያዎቹ ላይ ከተፃፉ መልዕክቶች መካከል 'ጂያን ሉ ዚ' የተሰኘ ፅሑፍ ይገኝበታል። የዚህ ፅሑፍ ትርጉም በርካሽ ዋጋ ዕቃ መግዛት ነው።

ድርጅቱ በማስታወቂያው ላይ 'ሻይ ልገዛ ሄጄ በርካታ ቆነጃጅት አየሁ። እናንተም እንደኔ ከገጠማችሁ ለጓደኞቻችሁ አሳውቁ - በርካሽ ዋጋ አገኘሁ' ሲል አስነግሮ ነበር።

በቻይና ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ አንድ ኩባያ ከተሰራጨ በኋላ ነው ከፍተኛ ትችት የጎረፈው።

"ይህ አስቀያሚ የሽያጭ ሂደት ነው" ነው ሲል አንድ ግለሰብ ፅፏል።

"በጣም የሚያስቀይመው ኩባያዎቹ ላይ የተፃፈው ነገር ብቻ ሳይሆን የተጠቀሙት ዓረፍተ-ነገር ነው" በማለት ሌላ ተጠቃሚ አክሏል።

ኩባንያው ከገጠመው ትችት በኋላ ረዘም ያለ ይቅርታ ያዘለ መግለጫ አውጥቷል።

"በቻንግሻ ያሉ ሰዎች እንኳ ያልተቀበሉት አግባብነት የሌለው መልዕክት ለቀናል። ይህ እጅግ አሳፋሪ ነው። እኛ ሴቶችን የማንቋሸሽ ምንም ዓይነት ዓላማ የለንም" ይላል መግለጫው።

ተጠቃሚዎች ሴክሲ ቲ የተሰኘው ትኩስ መጠጥ አቅራቢ መሰል ፆታ የሚያንቋሽሹ መልዕክቶች ሲያሰራጭ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ሲሉ ይተቻሉ።

ቻይና ውስጥ ያሉ ድርጅቶች መሰል ትችት ሲገጥማቸው ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከዚህ በፊት አንድ የልብስ ሳሙና ማስታወቂያ ጥቁር ጠል የሆነ መልዕክት አስተላልፏል ተብሎ ዓለም አቀፍ ትችት አስተናግዶ ነበር።

በማስታወቂያው ላይ አንዲት ቻይናዊት አንድ ጥቁር ግለሰብን ወደ ልብስ ማጠበያ ማሽን ከታው የቆዳ ቀለሙ ተቀይሮ ሲወጣ ያሳያል።