የማልኮም ኤክስ ግድያ ዳግም እንዲጣራ የቤተሰብ አባላት ጠየቁ

ታትሟል

ታዋቂው አሜሪካዊ ጥቁር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስ ሴት ልጆች አዲስ መረጃ መገኘቱን ተከትሎ የአባታቸው ግድያ ምርመራ እንደ አዲስ እንዲከፈት ጠይቁ።

ማልኮም ኤክስ በ1965 በተገደለ ወቅት የፖሊስ መኮንን የነበሩ ሰው በቅርቡ ሞተዋል።

ሰውዬው ከመሞታቸው በፊት ባሰሙት ኑዛዜ ምናልባት የአሜሪካው ወንጀል ምርመራ ቡድን ኤፍቢአይና ፖሊስ ግድያውን ሳይፈፅሙት እንዳልቀረ ተናግረዋል።

ሬይመንድ ውድ የተሰኙት ፖሊስ በወቅቱ ሥራቸው የነበረው የማልኮም ኤክስ ጠባቂዎች ከቀናት በፊት እንዲታሠሩ ማድረግ እንደነበር ተሰምቷል።

ማልኮም ኤክስ ኒው ዮርክ - ማንሃታን ውስጥ ከመገደሉ በፊት ጠባቂዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር አይዘነጋም።

በማልኮም ኤክስ ግድያ ምክንያት ሶስት ሰዎች ጥፋተኛ ተብለው ተፈርዶባቸዋል።

ሶስቱም ሰዎች ኔሽን ኦፍ ኢስላም የተሰኘው ፖለቲካዊና ኃይማናዊ ንቅናቄ አባላት ነበሩ።

የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸው አንደኛው እሥር ቤት ሳለ ሕይወቱ ሲያልፍ ሁለቱ ደግሞ ከዘመናት በኋላ በአመክሮ ተፈተዋል።

ማልኮም ኤክስ የኔሽን ኦፍ ኢስላም ንቅናቄ ቁንጮ ሰው ነበር። በወቅቱ ጥቁሮች ተገንጥለው ብቻቸውን መኖር አለባቸው ብሎ ያምን ነበር።

ነገር ግን ንቅናቄውን ጥሎ ከወጣ በኋላ በተለይ ደግሞ የተገደለ ሰሞን ለዘብ ያለ አቋም እንደነበረው ይነገራል።

ቢሆንም ማልኮም በጥቁሮች አንድነት፣ ለራስ ክብር መስጠት እንደ ራስን መቻል በመሳሰሉ ሐሳቦች ላይ ጠንከር ያለ አቋም የነበረው ሰው ነው።

የፖሊሱ ደብዳቤ ምን ይላል?

ደብዳቤው እንደሚለው የኒው ዮርክ ፖሊስ እና ኤፍቢአይ የካቲት 21 1965 የተደረገውን ግድያ ዝርዝር መረጃዎች ሸፋፍነዋል።

የፖሊሱ ጠበቃና ቤተሰቦች እንደሚሉት ግድያው በላይኛው ማንሃታን ሃርለም ውስጥ ሲፈፀም የፖሊስና ኤፍቢአይ ሤራ ሳይኖርበት አይቀርም።

ፖሊሱ እንደፃፈው ደብዳቤ ከሆነ በወቅቱ ሥራው የነበረው ለሕዝብ ንግግር በሚያሰማበት አዳራሽ ምንም ዓይነት ጥበቃ እንዳይኖረው ማድረግ ነበር።

ዕሑድ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፖሊሱ ቤተሰቦች ረይመንድ ውድ በምን ምክንያትና መች እንደሞተ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ነገር ግን ደብዳቤውን ከሞቱ በፊት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ያልፈለገው ከባለሥልጣናት ጫና እንዳይመጣበት ፈርቶ መሆኑን ተናግረዋል።

"በዚህ ግድያ ዙሪያ የሚገኝ የትኛውም ዓይነት መረጃ በደንብ ሊመረመር ይገባዋል" ብላለች ከማልኮም ኤክስ ልጆች መካከል አንዷ ኢልያሽ ሻባዝ።

ይህን ተከትሎ የኒው ዮርክ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ "ከወራት በፊት የማንሃታን ቀጣና ምርመራውን እንደ አዲስ አካሂዶ በማልኮም ኤክስ ግድያ ጉዳይ ሁለት ብይኖች ሰጥቷል።"

"የኒው ዮርክ ፖሊስ ያገኛው ጠቃሚ መረጃዎች ለማንሃታን አቃቤ ሕግ አስተላልፏል። ፖሊስ በየትኛው መንገድ እርዳታውን ለመለገስ ዝግጁ ነው" ብሏል።

ኤፍቢአይ ግን እስካሁን ድረስ ምንም አላለም።