የብራዚል የማፊያ ቡድን መሪ ከቁም እስር አመለጠ

አንድሬ ኦሊቪዬራ ማሴዶ

የፎቶው ባለመብት, Globo

የምስሉ መግለጫ, አንድሬ ኦሊቪዬራ ማሴዶ
ታትሟል

የብረዚል ትልቁ የማፊያ ቡድን መሪ ከእስር ቤት ወጥቶ በቁም እስር እንዲቆይ ተወስኖ ከእስር ቤት እንደወጣ የገባበት ጠፍቷል።

አንድሬ ኦሊቪዬራ ማሴዶ ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት የብራዚል እስቤት የወጣው ቅዳሜ ዕለት ነበር።

ይሁን እንጂ አንድሬ ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት እንዲወጣ የተሰጠው ትዕዛዝ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ተቀልብሶ ወደ እስር ቤቱ እንዲመለስ ቢታዘዝም የወንጀለኞች ቡድን መሪው የገባበት ጠፍቷል።

አንድሬ የሚመራው “ፊርድ ኮማንድ ኦፍ ዘ ካፒታል” የተሰኘው የወንጀለኞች ቡድን በብራዚል እና ፓራጓይ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ነው።

ወደ አውሮፓም ከፍተኛ መጠን ያለው ኮኬይን በድብቅ ያስገባል።

አንድሬ ከእስር ተለቆ በመኖሪያ ቤቱ በቁም እስር እንዲቆይ የተወሰነው ብዙ ካጨቃጨቀ በኋላ ነበር።

የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አንድሬ ከእስር ቤት ወጥቶ በመኖሪያ ቤቱ በቁም እስር እንዲቆይ የወሰኑት ፍርድ ሳይሰጠው በእስር ቤት ከሕግ ውጪ በርካታ ጊዜያን በማሳለፉ ነበር።

አንድሬ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር።

የሳኦ ፖሎ ግዛት አስተዳዳሪ አንድሬ ከእስር ወጥቶ በመኖሪያ ቤቱ በቁም እስር እንዲያሳልፍ መወሰኑ እጅጉን እንዳበሳጫቸው ተናግረው ነበር። ይህ ተቀባይነት የሌለው አደገኛ ወንጀለኞችን አቅልሎ ማየት ነው ብለውም ነበር።

ይሁን እንጂ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ውሳኔ ተቀልብሶ ወደ እስር ቤት እንዲመለስ ቢወሰንም የብራዚል ፖሊስ አንድሬን ፈልጎ ሊያገኘው አልቻለም።

አንዳንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አንድሬ ከአገር ወጥቶ መሸሹን እየዘገቡ ይገኛሉ። ፖሊስ ግን ስለ ምርመራ ሂደቱ ያለው ነገር የለም።