የትራፊክ አደጋ ፡ በታይላንድ አውቶብስ ከባቡር ጋር በመጋጨቱ በደረሰ አደጋ ቢያንስ 18 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በታይላንድ አንድ አውቶብስ ከባቡር ጋር በመጋጨቱ በደረሰ አደጋ ቢያንስ 18 ሰዎች ሲሞቱ፤ በርካቶች መጎዳታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

አደጋው ያጋጠመው በምስራቅ ባንኮክ 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ እሁድ እለት ጠዋት ነው።

ፖሊስ እንዳለው በአውቶብሱ ውስጥ የነበሩት መንገደኞች ለቡድሂዝም ሃይማኖት ክብረ በዓል ወደ ቤተመቅደስ እያመሩ ነበር።

አደጋው ሲዳርስ በአውቶብሱ 60 መንገደኞች ተሳፍረው እንደነበር የግዛቷ አስተዳዳሪ ሜትሪ ትሪቲላኖንድ ተናግረዋል።

ከስፍራው የወጡ ምስሎችም አውቶብሱ ወደ ጎን ተገልብጦ በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱንና እቃዎችም በባቡሩ ሃዲድ ላይ ተበታትነው አሳይተዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አውቶብሱን ለማንሳት ክሬን እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

የሟቾቹ ቁጥርም ሊጨምር ይችላል ተብሏል።

የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕራዩት ቻን ኦ ቻ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀው፤ የአደጋው ምክንያት ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

በታይላንድ የተሽከርካሪዎች ግጭት የተለመደ ሲሆን፤ ለዚህም የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎችና የተጨናነቁ መንገዶች ዋናኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ይታመናል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከሁለት ዓመታት በፊት ባወጣው ሪፖርት ታይላንድ በትራፊክ አደጋ በሚሞቱ ሰዎች ሰዎች ከዓለም አገራት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ከሁለት ዓመታት በፊት መጋቢት ወር ላይ በሰሜን ምስራቅ ታይላንድ አንድ አውቶብስ መንገድ ስቶ ከዛፍ ጋር በመጋጨቱ ቢያንስ 18 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ በርካቶች ለጉዳት ተዳርገው ነበር።

ከአራት ዓመታት በፊትም አንድ ባቡር ጎብኝዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ ከነበረ ባለፎቅ አውቶብስ ጋር ተጋጭቶ በደረሰ አደጋ በትንሹ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።