ኮሮናቫይረስ ፡ የትራምፕ በኮቪድ መያዝን አጠራጣሪ የሚያደርጉ 5 ጉዳዮች

ትራምፕ መኪና ውስጥ
ታትሟል

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና ቀዳማዊ እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ የኮሮና ተህዋሲ እንደተገኘባቸው ከተገለጸ ዛሬ አምሰተኛ ቀናቸው ነው።

ሁለቱም ሆስፒታል ገብተው ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል። ትራምፕ እሑድ አላስችል ብሏቸው ከሆስፒታል ወደ ደጅ ወጥተው ደጋፊዎቻቸውን ሰላም ብለው ሹልክ ብለው ተመልሰዋል።

ሐኪሞቸውም "ፕሬዝዳንቱ ሰኞ ማታ ከሆስፒታል ወጥተው ወደ ዋይት ሐውስ ሊያቀኑ ይችላሉ" እንዳሉት በሄሊኮፕተር ከዋልተር ሪድ የህክምና ማዕከል ወጥተው ወደ ጽህፈት ቤታቸው ተመልሰዋል።

የትራምፕን በኮሮናቫይረስ መያዝን ተከትሎ እያንዳንዷ ደቂቃ አዳዲስ ዜና ይዛ እየመጣች ነው። መግለጫዎች ተከታትለው ቢወጡም እርስበርስ መጣረሳቸው አልቀረም። አንዳንዶቹን ተመልክተናቸዋል።

1.ትራምፕ ለመጨረሻ ጊዜ ተህዋሲው የለብህም የተባሉት መቼ ነው?

ዋይት ሐውስ መቼ ነው በትክክል ትራምፕ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ያወቀው የሚለው በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው።

በሌላ ቋንቋ ከተህዋሲው ነጻ ነህ የተባሉት ለመጨረሻ ጊዜ መቼ ነበር?

ቅዳሜና እሑድ በነበሩ ተከታታይ የጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ የዋይት ሐውስ የሐኪሞች ቡድን በጋዜጠኞች አንድ መሠረታዊ ጥያቄ በተደጋጋሚ ተጠይቋል።

መቼ ነው ዶናልድ ትራምፕ ለመጨረሻ ጊዜ ከተህዋሲው ነጻ መሆናቸውን ያወቁት?

ዋይት ሐውስ የሚለው ሐሙስ ማታ ፕሬዝዳንቱን አመም አድርጓቸው ነበር። የዚያኑ ዕለት ምሽትም ተህዋሲው እንዳለባቸው አወቁ። ሌሊት ላይ በትዊተር ሰሌዳቸው ይህንኑ ለአሜሪካ ሕዝብ ይፋ አደረጉ።

ዎልስትሪት ጆርናል ግን ይህንን የሚቃረን ዘገባ አውጥቷል።

ትራምፕ ፎክስ ኒውስ ላይ በቀጥታ የስልክ ቃለ ምልልስ ገብተው "ውጤት እየጠበቅኩ ነው" ሲሉ በተህዋሲው መያዛቸውን አሳምረው ያውቁ ነበር።

ለምን ታዲያ ምስጢር ማድረግ ፈለጉ? ምናልባት ውጤቱ በ2ኛ ምርመራ እንዲረጋገጥ ስለፈለጉ ይሆን? ምናልባት ሌላ የፖለቲካ ግብ ነበራቸው?

በትራምፕ ጉዳይ ብርቱ ጥያቄ ሲነሳ ቁጣ የሚቀናት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ኬይሊ ማክኔኒ አላፈናፍን ያሏት ጋዜጠኞችን "ማኅተም ያረፈበትን የያንዳንዱን ደቂቃና ሰኮንድ የፕሬዝዳንቱን የምርመራ ዝርዝር ላድላችሁ አልችልም" ብላለች። ይህን ያለችው እሑድ ማታ ነበር።

የአሜሪካ ሊበራል ሚዲያ ጋዜጠኞች ግን በዋዛ የሚደነብሩ አይደሉም። በጥያቄ ነክሰው ከያዙ ያዙ ነው።

ጥያቄያቸውን አጥብቀው ደገሙላት። መቼ ነው ፕሬዝዳንቱ በትክክል መያዛቸውን ያወቁት?

"ፕሬዝዳንት ትራምፕ በየጊዜው ምርመራ ያደርጋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ተህዋሲው አለብህ የተባለው ከቤድሚኒስትር የተመለሰ ዕለት ነው፤ ሐሙስ" ብላለች ማክኔኒ።

ቤድሚኒስተር በኒው ጄርሲ የሚገኝና ንብረትነቱ የትራምፕ የሆነ የጎልፍ ሜዳና የባለጸጎች መንፈላሰሻ ስፍራ ነው። እዚያ ግቢ ሐሙስ የገቢ ማሰባሰብያ ትዕይነት ነበር። ትራምፕ የተገኙበት መሰናዶ።

ይህን ካልን ዘንዳ ቀኑ ለምን ያወዛግባል? መቼስ ቢሆን ምን ለውጥ አለው? የሚለውን እንመርምር።

ዶክተር ሾን ኮንሊ የፕሬዝዳንቱ የግል ሐኪም ነው። ቅዳሜ ዕለት መግለጫ ሲሰጥ አንድ ነገር ሳት አለው።

ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው የትራምፕ የቅርብ ሰዎች

የፕሬዝዳንቱ ውጤት የመጣው "ከ72 ሰዓታት በፊት ነበር" ብሎ ተናገረ።

ይህ ማለት ከቅዳሜ 72 ሰዓት ወደ ኋላ መቁጠር ነው። እንቁጠር? ሄደን ሄደን ረቡዕ ላይ እናርፋለን። ይህም ማለት ትራምፕ በሜኔሶታ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በተህዋሲው መለከፋቸውን ያውቁ ነበር ማለት ነው።

አውቀው ይሆን ዝም ያሉት? ቅስቀሳው እንዳይስተጓጎል ፈልገው ቢሆንስ?

የትራምፕ ቀንደኛ ተቀናቃኝ ሚዲያዎች ነገሩን አራገቡት።

ዋይት ሐውስ በፍጥነት ማስተካከያ መግለጫ አውጣ። ሐኪሙ ተሳስቶ ነው "72 ሰዓት ያለው"፣ "የአፍ ወለምታ ነው" አለ።

ሆኖም ብዙዎች ትራምፕን አላመኗቸውም። የዋይት ሐውስንም ማስተባበያ ለማመን ተቸግረዋል።

የሲኤንኤኑ የጤና ጉዳዮች ዘጋቢ ዕውቁ ዶ/ር ሳንጄ ጉፕታ እንደሚለው ትራምፕ ተህዋሲው ያዛቸው ከተባለ በኋላ ጤናቸው በነገታው ማሽቆልቆሉ የሚነግረን አንድ ምስጢር አለ። ይህም ሰውየው መጥፎውን ዜና ከሰሙ ሰንበትበት ማለታቸውን ነው።

2.ትራምፕ በጠና ታመዋል ወይስ እየዋሹን ነው?

እንኳንስ ሚዲያዎች ዋይት ሐውስና ሐኪሞቻቸውም በትራምፕ ጤና ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ነገር አያወሩም።

አርብ ዕለት ትራምፕ መጠነኛ የኮቪድ-19 ምልክቶችን እያሳዩ ነው ተባልን። በኋላ ላይ የወጡ መረጃዎች ደግሞ ትኩሳት ጀምሯቸዋል የሚሉ ነበሩ።

ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ ያንኑ ቀን መተንፈስ ተቸግረው ነበር የሚሉ መረጃዎች ወጡ።

ቅዳሜ ዕለት ዶ/ር ኮንሌይ ለጋዜጠኞች ትራምፕ በጣም ደህና ናቸው አሉ። እሳቸውን ጤና የሚከታተለው የሒኪሞች ቡድን በትራምፕ ጤና በጣም ደስተኛ ሆኗል ሲሉ ደመደሙ።

ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ግን የዋይት ሐውስ ቺፍ ኦፍ ስታፍ ማርክ ሚዶውስ የትራምፕ ጤና አሳሳቢ ሆኗል አሉ።

እንዴት ሁለቱ የተጣረሰ መግለጫ ሰጡ? ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ ይሆን?

Trump's health team press

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የፕሬዝደንት ትራምፕ ሐኪሞች መግለጫ ሲሰጡ

3.ትራምፕ የሚወስዱት መድኃኒት የትኛው ነው?

ሌላው የተዘበራረቀ መግለጫ የተሰጠበት ጉዳይ ትራምፕ እየወሰዷቸው ነው በተባሉ መድኃኒቶች ዝርዝር ነው።

ዶ/ር ኮንሌይ እሑድ ዕለት በሰጡት መግለጫ ትራምፕ ዴክሳሜታዞን እየወሰዱ እንደሆነ ተናገሩ። ይህ መድኃኒት አንድ ሰው በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ካልሆነ የሚሞክረው መድኃኒት እንዳልሆነ ይታወቃል።

ዶ/ር ኮንሌይ ጨምረው እንደተናገሩት የትራምፕ የኦክሲጂን መጠን ጤነኛ ሰው ሊኖረው ከሚገባው ዝቅ ብሎ ነበር። ወደ 93 በመቶ ደርሶም ነበር። ይህ ማለት ትራምፕ በኦክሲጅን እርዳታ ነበር የሚተነፍሱት።

ይህ መግለጫ ቀደም ሲል የወጡ መግለጫዎችን የሚንድ ሆኗል። ምክንያቱም ትራምፕ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ ተብሎ በተደጋጋሚ ሲነገር ነበር።

የተጠቀሰውን መድኃኒት የሚያውቅ ግን ትራምፕ ሞትን በሩቁ አይተው ነበር የተመለሱት ቢል አልተሳሳተም።

ትራምፕ ዕድሜያቸውም ሆነ ክብደታፈቸው ገፍቷል። 74 ደርሰዋል በእድሜ፣ ኪሏቸው በግልጽ ባይታወቅም አለመጠን ውፍረት ካለባቸው ሰዎች ተርታ የሚመደቡ ናቸው። እንዲህ ባለ ሁኔታ ያሉ ሰዎች ደግሞ ኮቪድ-19 የሚጨክንባቸው ሰዎች ናቸው።

ትራምፕ እየወሰዱት ይገኛሉ የተባለው ሌላው መድኃኒት ለኢቦላ ታማሚዎች የሚሰጠው ነው። ለኮሮናቫይረስ ግን በሙከራ ደረጃ ያለ ነው። ስሙ ሪምዴሲቬር ይባላል። በከፍተኛ ሁኔታ በኮቪድ-19 ለታመሙ የስቀይ ጊዜን ያሳጥራል ይሉታል።

ይህን መድኃኒት ለመውሰድ 5 ቀናት በከፍተኛ ማገገሚያ ውስጥ መቆየት ያሻል። ትራምፕ ግን እነዚህን ከባባድ መድኃኒቶች እየወሰዱ ደጋፊዎቻቸውን ሰላም ብለው የሚመለሱት እንዴት ነው?

በዚህ ሐዘን በተጫነው ሁኔታ ፈገግታን የሚጭረው ግን ፕሬዝዳንቱ የመድኃኒት ኮክቴይል እያነሱ ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት እጅግ ያቀነቅኑለት የነበረው የወባ መድኃኒት 'ሐይድሮክሲክሎሮኪዩን' እንደ ዲዘርትም እንደ አፕታይዘርም አለመቅረቡ ነው።

4.ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ራሳቸውን ለምን አላገለሉም?

የትራምፕ ምክትል ማይክ ፔንስ ግን ተህዋሲው እንዳልነካቸው ከአንዴም ሁለት-ሦስቴ አረጋግጠዋል። ሆኖም ከፕሬዝዳንቱ ጋር በቅርበት ይገናኙ ነበር።

ማይክ ፔንስና ባለቤታቸው ካረን ለ3ኛ ጊዜ ተህዋሲው የለባችሁም የተባሉት እሑድ ነው። ይህ ግን ቢሮ እንዲገቡ፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ፣ ከሰዎች ጋር በቅርብም በሩቅም እንዲገናኙ፣ ዕለታዊ ተግባራቸውን እንዲወጡ አይፈቅድላቸውም።

ምክንያቱም ተህዋሲው በተለምዶ ጡንቻ ለማውጣት አምሰት ቀናትና ከዚያ በላይ ይፈልጋል።

ለዚህም ነው ሰዎች ከተህዋሲው ጋር ንክኪ ከነበረው ሰው ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተገናኝተው ከታዩ በትንሹ ለ14 ቀናት ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚገደዱት።

የታላቋ አሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ግብረ ኃይል የበላይ ጠባቂና አለቃ ማይክ ፔንስ እንዴት ራሳቸው ላወጡት ደንብና ትዕዛዝ አይገዙም?

ሴናተር ማይክ ሊ

የፎቶው ባለመብት, Evn

የምስሉ መግለጫ, ሴናተር ማይክ ሊ

5. ከትራምፕ ጋር የተገናኙ ሰዎች ለምን ቸልተኛ ሆኑ?

ባለፈው ቅዳሜ ትራምፕ በዋይት ሐውስ አጸድ እንግዳ ነበራቸው፤ ጥቁር እንግዳ።

ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያጯት ኤሚ ኮኒ ባሬት። እሷን በይፋ ለማጨት የተጠራው ሰው ብዙ ነው።

ከቁልፍ የሪፐብሊካን ሰዎች መካከለም የቀረ የለም።

ያን ዕለት ሰዎች ሲስቁ፣ ሲጫወቱ፣ ሲተቃቀፉና ሲሳሳሙ ነበር። ምናልባት ያን ቀን የተደገሰው ለኮኒ ባሬት ብቻ አልነበረም። ለኮቪድ-19ም ጭምር ነበር።

በዚያ ግብዣ ጭምብል ያጠለቁ ጥቂትሰዎች ነበሩ። ከምክትል ፕሬዝዳንት ፔንስ ጎን የተቀመጡ አምሰት ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። ፔንስ እንዴት ተረፉ?

ለነገሩ ተረፉ የሚባለው ከ14 ቀናት በኋላ ነው።

ከዚህ ለኮኒ ባሬት ከነበረው ደግስ በፊትም ሌላ ጉድ አለ።

ባለፈው በወዲያኛው ሳምንት እሑድ፣ ሰኞና ማክሰኞ ትራምፕ ከባይደን ጋር ለነበረባቸው የማክሰኞ ክርክር ዝግጅት በርካታ ሰዎችን እያገኙ ነበር። በስብሰባ ተጠምደው ነበር። ለዚህ ክርክር ደፋ ቀና ይሉ የነበሩ ሰዎች አራቱ ተህዋሲው ተገኝቶባቸዋል።

ይህ ሌላ ጥርጣሬን ፈጥሯል። ትራምፕ ሐሙስ ሳይሆን ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ ይሆን ተህዋሲው የነካቸው? ከሆነ ለምን ደበቁን?

የፕሬዝዳንቱ የምረጡኝ ቅስቀሳ መሪ ቢል ስቴፒን፣ የቀድሞው የኒው ጀርሲ ገዢ ክሪስ ክሪስቲ እና የትራምፕ ቀኝ እጅ ሆፕ ሂክስ ሁሉም የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

በእነዚህ ስብሳባዎች ተሳትፈው ተረፍን ያሉት የቀድሞ የኒውዮርክ ከንቲባ ሩዲ ጁሊያኒ፣ የትራምፕ አማካሪ ስቴፈን ሚለር እና ጃሰን ሚለር ብቻ ናቸው።

የእነሱም ነገር የሚረጋገጠው ከ14 ቀናት በኋላ ነው። እሱም አርፈው ከተቀመጡ ነው።

ይህ ሁሉ ንክኪና ትርምስ ባለበት ሁኔታ ግን ዋይት ሐውስ ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች እግር በእግር እየተከታተለ ቫይረሱን ለመቆጣጠር አንዳችም ሙከራ ሲያደርግ አለመታየቱ ሌላ ጥርጣሬን ፈጥሯል።

ዋሺንግተን ፖስት እንደዘገበው የዋይት ሐውስ ሠራተኞችም እምብዛምም የተለየ የጤና መመርያ አልደረሳቸውም።

በንክኪ ደረጃ የነበሩ ሰዎችም ራሳቸውን እንዲያገሉ አልተደረገም። ለምን?

እርግጥ ነው ለአሜሪካዊያን በኮቪድ-19 መሞት ብርቅ አይደለም። እስካሁን ድረስም ከ209 ሺህ ሰዎች በላይ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በተህዋሲው ሲሳለቁ የነበሩት የአገሪቱ ቁልፍ ሰው በቫይረሱ መያዝና የተጣረሱ መረጃዎች መውጣት ሰውየው በእርግጥ በተህዋሲው ተይዘዋልን ወይስ ሁሉም ነገር ድራማ ነው የሚሉም አልጠፉም።

እንዴት በመሣሪያ እርዳታ ሲተነፍስ ነበር የተባለ ሰው በነገታው ድኖ ደጋፊዎቹን ለማየት ይወጣል? ያልተነገረ ነገር ይኖር ይሆን?