ሃይማኖት፡ ፈረንሳይ በሙስሊም ማህበረሰቧ ላይ ልታወጣው ያሰበችው ሕግ ምንድን ነው?

ታትሟል

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን 'እስላማዊ ተገንጣዮች' ያሏቸውን ለመከላከልና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለመጠበቅ የሚያስችል ጥብቅ ሕግ ለማውጣት መታቀዱን አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው ንግግራቸው፤ በፈረንሳይ የሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውና 6 ሚሊዮን የሚገመቱ ሙስሊሞች ከሌላው ማሕበረሰብ የተለየ 'ተቃዋሚ ማህበረሰብ' የመመስረት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን ለመከላከል በወጣው ረቂቅ ሕግ፤ ለትምህርት ቤቶችና ለመስጊዶች የሚደረግ የውጭ ድጋፍን መቆጣጠር የሚለው ይገኝበታል።

ይሁን እንጅ አንዳንዶች ፕሬዚዳንቱ በፈረንሳይ ያሉ ሙስሊሞችን ለመጨቆን እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።

በፈረንሳይ የሃይማኖት ሕግ መሰረት መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ በሕግ ይከለከላል ።

ይህ ሕግ ማንኛውም ሃይማኖትም ሆነ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ከሕግ ፊት እኩል ናቸው ይላል።

አገሪቷ በምዕራብ አውሮፓ ከሚገኙ አገራት በርካታ ሙስሊም ማህበረሰብ ያላባት አገር ናት።

በመሆኑም በርካቶች መንግሥት ሙስሊሞቹን ኢላማ ለማድረግ ሃይማኖትን ተገን አድርጓል ሲሉ ቅሬታ ያሰማሉ።

ለዚህም አንደ አንድ ምሳሌ የሚጠቅሱት ፊትን የሚሸፍነው ኒቃብ መልበስ መከልከሉን ነው።

ፕሬዚዳንቱ አርብ ዕለት ባደረጉት ንግግር "እስላማዊ ተገንጣዮች ለፈረንሳይ አደገኛ ናቸው፤ ምክንያቱም የራሱ ሕግ ስላለው ብዙ ጊዜ ተቃዋሚ ማሕበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል" ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ እንዲህ አይነቱ መነጠል ደግሞ ሕፃናት ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ እንዲሆን ከስፖርት፣ ከባህልና ሌሎች የማህበረሰብ እንቅስቃሴዎች ውጭ ያደርጋቸዋል ሲሉም አክለዋል።

በመሆኑም ፕሬዚደንቱ ሕግ ለማውጣት ያቀረቧቸው ረቂቅ ሃሳቦች በዓመቱ መጨረሻ ላይ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርቡ ተገልጿል። የቀረበው ረቂቅ ሃሳብ የሚከተሉትን ያካትታል።

  • የስፖርት ድርጅቶችና ሌሎች ማህበራት እስላማዊ አስተምህሮት መስጫ እንዳይሆኑ መቆጣጠር
  • ከውጭ አገር የሚመጡ ኢማሞችን [የሃይማኖት መሪዎች] ወደ ፈርንሳይ እንዲገቡ የሚፈቅደውን ሥርዓት ማብቃት
  • ለመስጊዶች የሚደረገውን ድጋፍ መቆጣጠር
  • የቤት ውስጥ የሚሰጥ ትምህርትን መገደብ

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሃይማኖት መሪዎች እና ምሁራን ጋር ለወራት ምክክር ሲደረግበት መቆየቱም ተገልጿል።

ፈረንሳይ ለስደተኛ ማህበረሰቦች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ድጋፍ ለመስጠት እንደምትሰራ በመግለፅ፤ ይህም ያለውን ክፍተት እንደሚሞላ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

በርካቶች ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ ከሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በፊት የቀኝ ክንፍ ድምፅ ሰጭዎችን ለመስበክ የተደረገ ሙከራ እንደሆነ ተመልከተውታል ተብሏል።

አንዳንድ ሙስሊሞችም ፕሬዚደንቱ ባቀረቡት ረቂቅ ሃሳብ ላይ ቁጣቸውን ገልፀዋል።

የፈረንሳይ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ያሰር ሎውቲ በትዊተር ገፁ ላይ " ሙስሊሞችን መጨቆን ስጋት ነበር። አሁን ደግሞ ተስፋ ሆኗል" ሲል አስፍሯል።