አሜሪካ፡ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የግል ዶክተር ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, BRENDAN SMIALOWSKI
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ የአንድ ሰው ስም የህዝቡን ቀልብ ገዝቷል- ዶክተር ሾን ኮንሊ
የአርባ አመቱ የፕሬዚዳንት ትራምፕ የግል ዶክተር የዋይት ሃውስም ዶክተርነት ማዕረግን አግኝተዋል።
ዶክተሩ በዋይት ሃውስ ዶክተርነት የተቀጠሩት ከሁለት አመታት በፊት ነው።
ለዚህ ስፍራ ታጭተው የነበሩት የአሜሪካው የቀድሞ ሰራዊት አባላት ጉዳዮች ቢሮን እንዲመሩ የተመረጡት ሮኒ ጃክሰን ነበሩ።
በተለያዩ ውንጀላዎች ምክንያትም ዶክተር ጃክሰን ከእጩነት ራሳቸውን አገለሉ።
ዶክተር ኮንሊ አማራጭ የህክምና መንገዶችን በመጠቀም ይታወቃሉ።
ለሰው ልጅ መድኃኒቶች ብቻ ሳይሆኑ ግላዊ ህይወት፣ አመጋገብና የከባቢ ሁኔታም ከፍተኛ ተፅእኖ ስለሚያሳርፉ እነሱን በሙሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁለገብ የሆነ ህክምናን በመጠቀምም ይታወቃሉ።
ሁሉን አቀፍ፣ ኦስቴዮፓቲክ በሚባለው የህክምና ዘርፍም እውቅናን ማትረፍ ችለዋል።
በዋይት ሃውስ ዶክተርነት ከመቀጠራቸው በፊትም በባህር ኃይልም ውስጥ በድንገተኛ ህክምና ዶክተርነት አገልግለዋል።
በመቀጠልም በአፍጋኒስታን በሚገኘው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት፣ ኔቶ ሆስፒታልም ሰርተዋል።
በፔኒስልቫኒያ የተወለዱት ዶክተር ኮንሊ በባለፈው አመትም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለወባ በሽታ ፈውስ የሆነውን ሃይድሮክሲክሎሮኪን መውሰድ መጀመራቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎም የበርካታ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች ሃይድሮክሲክሎሮኪን የኮሮናቫይረስ በሽታ መድኃኒት ነው ቢሉም እስካሁን ድረስ በህክምና የተደገፈ ማስረጃ አልተገኘም።
ሆኖም የትራምፕ ዶክተር፣ ዶክተር ኮንሊ ሃይድሮክሲክሎሮኪን ከጎንዮሽ ጉዳቱ በበለጠ ጥቅሙ ይበልጣል ብለው ነበር። በትናንትናው ዕለት ግን ትራምፕ ይህንን መድኃኒት አይወስዱም ብለዋል።












