ኮሮናቫይረስ፡ በዩናይትድ ኪንግደም ከ10ሺህ በላይ ተጨማሪ ሰዎች በኮቪድ -19 መያዛቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ኪንግደም በስፋት ምርመራ ማካሄድ ከጀመረች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ10 ሺህ ሰዎች በላይ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን አስታወቀች።
በአገሪቷ ላለፉት 28 ቀናት በተደረገ ምርመራ 12 ሺህ 872 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ የ49 ሰዎች ሕይወትም አልፏል።
በቴክኒክ ችግር ምክንያት በዚህ ሳምንት የተወሰኑ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ያልተመዘገበ ቢሆንም በቅዳሜ ዕለቱ መረጃ ላይ እንደተካተተ መንግሥት ገልጿል።
መንግሥት ይህን ያለው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የወጣው መረጃ የቫይረሱ ስርጭት ቀድሞ ከነበሩት ሳምንታት ቀስ በቀስ ሊጨምር እንደሚችል ካመላከተ በኋላ ነው።
መረጃው በኢንግላንድ ምን ያህል ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ለማወቅ ከማሕበረሰቡ ውስጥ በተወሰደ የአጋጣሚ ናሙና ላይ በተደረገ ሳምንታዊ ምርመራ ላይ የተመሰረተ ነበር።
የአገሪቷ መንግሥት በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎችም የቫይረሱ ሥርጭት ያለበትን የቅርብ ሁኔታ ስለሚያሳዩ በየዕለቱ የሚመዘገቡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥርም በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብሏል።
ይሁን እንጅ በሚቀጥሉት ቀናት የሚወጣው መረጃ በቀደመው ሳምንት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን እንደሚያካትት አሳስቧል።
የጤና መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ መረጃው በዚህ መልኩ መውጣቱ ሰዎች የምርመራ ውጤታቸውን ከመቀበል አያግዳቸውም ብለዋል። ውጤታቸውም በተለመደው አግባብ እንደሚገለፅላቸው ቃል አቀባዩ አክለዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም እስከ ቅዳሜ እለት ድረስ 480 ሺህ 017 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በዩናይትድ ኪንግደም የታየው የቫይረሱ ሥርጭት መስፋፋትም በሌሎች የአውሮፓ አገራት ላይ ታይቷል።
ፈረንሳይ ቅዳሜ ዕለት 16 ሺህ 972 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም አዲስ የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።
በኔዘርላንድስ እና ቤልጂየም በቅደም ተከተል 3ሺህ 967 እና 3ሺህ 175 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ለአገራቱ ይህ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑ ተገልጿል።
በአውሮፓ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሩሲያም ከግንቦት ወዲህ ከፍተኛ የተባለውን 9 ሺህ 859 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መዝግባለች።
በተለይ በአውሮፓ ወረርሽኙ እንደገና እያገረሸ ነው።












