ኮሮናቫይረስ ፡ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Drew Angerer

ታትሟል

በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል የገቡት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ደህና መሆናቸውንና ቀጣዮቹ ቀናትም ለጤንነታቸው ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ጤንነታቸውን አስመልክቶ የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎችን ተከትሎ ቅዳሜ ምሽት በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ነው።

የፕሬዚደንቱ ሐኪምም ትራምፕ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ እና ሕክምናውን ከጀመሩ አንስቶ ለውጥ እንዳሳዩ ተናግረዋል።

ሐኪማቸው ዶ/ር ኮንሊ በሰጡት መግለጫ ላይ ፕሬዚደንቱ ከተጋረጠባቸው አደጋ ሙሉ ለሙሉ ባይላቀቁም፤ የሕክምና ቡድኑ ግን በሁኔታቸው ተስፋ እንዳለው ተናግረዋል።

ከሰዓታት በፊት ትራምፕ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ ያለ ከረቫት የሱፍ ኮት በሸሚዝ ለብሰው ታይተዋል። በንግግራቸውም በዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ በዋልተር ሪድ ብሔራዊ ወታደራዊ ሕክምና ማዕከል የሚሰሩ ዶክተሮችና ነርሶችን አመስግነዋል።

"እዚህ ስመጣ ደህና አልነበርኩም ፤ አሁን ላይ ግን እየተሻለኝ ነው" ብለዋል ትራምፕ። የሚቀጥሉት ቀናት ወሳኝ እንደሆኑ ገልፀው፤ " በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ምን እንደሚፈጠር እናያለን" ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ በኮቪድ-19 መያዛቸውን በትዊተር ገፃቸው ለሕዝብ ይፋ ያደረጉት ባሳለፍነው አርብ ነበር።

ይህም የምረጡኝ የቅስቀሳ ዘመቻቸውን ያቋረጠባቸው ሲሆን ከምርጫው በፊት አዲስ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ለመሰየም መሞከራቸው ላይም ጥርጣሬን አሳድሯል።

ትራምፕ በከሮናቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል ከገቡ ሁለተኛ ቀናቸውን ይዘዋል።

ስለ ትራምፕ ጤንነት የምናውቃቸው ነገሮች

ቅዳሜ ዕለት ጠዋት የፕሬዚደንቱ ሐኪም ዶ/ር ኮንሊ በሰጡት መግለጫ ለፕሬዚደንቱ ተጨማሪ ኦክስጅን አለመሰጠቱንና ለ24 ሰዓታትም ትኩሳት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ፕሬዚደንቱ ለመጭዎቹ 'ጥቂት ቀናት' በሆስፒታሉ እንደሚቆዩ ዋይት ሃውስ ገልጿል።

ዶ/ር ኮንሊ ስለትራምፕ የጤንነት ሁኔታ ሲናገሩም ተስፋ እንዳላቸው ገልፀው፤ ከሆስፒታል ሊወጡ የሚችሉበትን ጊዜ ግን አልገለፁም።

ሆኖም የዋይት ሃውስ ቺፍ ኦፍ ስታፍ (የቢሮ ኃላፊ) ማርክ ሚዶውስ፤ ፕሬዚደንቱ የማገገም ሂደት ላይ እንዳልነበሩ ጠቅሰው፤ ጤንነታቸው ላይ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።

ፕሬዚደንቱ ላለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የበሽታው ወሳኝ ምልክቶች እንደታዩባቸው በመግለፅም ቀጣዮቹ 48 ሰዓታት አስጊ እንደሚሆኑ አክለዋል።

የ74 ዓመቱ ትራምፕ እድሜያቸውና የሰውነታቸው ክብደታቸው ግዙፍ የሚባሉ ዓይነት በመሆናቸው ለኮቪድ-19 ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ይመደባሉ።

እስካሁን በሙከራ ላይ ያለ መድሃኒት እና የፀረ ቫይረስ መድሃኒት እየወሰዱ ነው።

ሐኪማቸው ቅዳሜ እለት በሰጡት መግለጫ ፕሬዚደንቱ ኦክስጅን ይወስዱ ነበር ወይ? ተብሎ በተደጋጋሚ ለተነሳላቸው ጥያቄ " በዚህ ሰዓት እየወሰዱ አይደለም ፤ አሁን ሁላችንም እዚህ ባለንበት ሰዓት ኦክስጅን አልተገጠመላቸውም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይሁን እንጅ በርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ፕሬዚደንቱ አርብ ዕለት ሆስፒታል ከመግባታቸው በፊት በዋይት ሃውስ ኦክስጅን ተገጥሞላቸው እንደነበር ዘግበዋል።

ቅዳሜ ምሽት በተሰጠው መግለጫ ግን የሕክምና ቡድኑ ትራምፕ 'ሬምዲሲቫየር' የተሰኘውን መድሃኒት ሁለተኛውን ዶዝ መጨረሳቸው ተገልጿል። ከሰዓቱንም በደህና ሁኔታ ሲያሳልፉ ነበር ተብሏል።

ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ እና በዋይት ሃውስ እረፍት እያደረጉ መሆናቸው ተነግሯል።

የምርጫ ዘመቻውስ?

ፕሬዚደንት ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ "ዘመቻውን በተጀመረበት መንገድ ለማጠናቀቅ በቅርቡ እመለሳለሁ ብየ አስባለሁ" ሲሉ ተስፋቸውን ገልፀዋል።

የፕሬዚደንቱ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ትራምፕ ወደ ምርጫ ዘመቻው መመለስ እስከሚችሉ ድረስ ባላቸው ፍጥነት ቅስቀሳውን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በመሆኑም አሁን ላይ የፕሬዚደንቱ ወንድ ልጆች ዶናልድ ጀር እና ኤሪክ እንዲሁም ምክትል ፕሬዚደንቱ ማይክ ፔንስ ዘመቻውን ያስቀጥላሉ ተብሏል።

የዘመቻው ቃል አቀባይም የመጀመሪያው ዝግጅት ሰኞ የሚካሄደው 'ቨርቹዋል'[ ኦንላይን] ሰልፍ እንደሆነ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

አርብ ዕለት ተመርምረው ከቫይረሱ ነፃ የሆኑት ምክትል ፕሬዚደንት ፔንስ የዴሞክራቲክ ምክትል ፕሬዚደንት እጩ ካማላ ሃሪስ ጋር ረቡዕ ክርክር ለማካሄድ ፕሮግራም ይዘዋል።

የዴሞክራቲኩ ጆ ባይደንም ዘመቻቸውን ቀጥለዋል። ቅዳሜ እለትም 'ቨርቹዋል' ዝግጅት አሰናድተዋል።

ትራምፕ ለወባ በሽታ ፈዋሽነቱ የሚታወቀውን ሀይድሮክሲክሎሮኪውን መድኃኒትን በተደጋጋሚ ሰዎች እንዲወስዱ ሲወተውቱ ነበር።

ከዚህ በፊት ይህንኑ መድኃኒት እንደወሰዱትና ጥሩ እንደሆነም ተናግረው ያውቃሉ።

አሁን እርሳቸው ሀይድሮክሲክሎሮኪውንን ወስደው ይፈወሱ ይሆን ወይ የሚለው የጠላትም የወዳጅም ጥያቄ ሆኗል።

ትራምፕ አሁን የሚወስዱት መድኃኒት ረምዴስቪር የተባለ ጸረ-ቫይረስ መድኃኒት ነው። ይህ መድኃኒት በኢቦላ ፈዋሽነቱ ይታወቃ።

የትራምፕ በተህዋሲው መያዝን ተከትሎ ሴናተሮችና ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዲሁም ረዳቶቻቸው ምርመራ ማድረግ ጀምረዋል።

እስከአሁን ምክትል ፕሬዝዳንቱና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተህዋሲው እንደሌለባቸው ተረጋግጧል። ሆኖም የቀድመው የፕሬዝዳንቱ አማካሪ ኬሌያን ኮንዌይ፣ ሁለት የሪፐብሊካን ሴናተሮች ማይክ ሊ እና ቶም ቲሊስ ቫይረሱ ተግኝቶባቸዋል።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ጉዳዮች ሥራ አስኪያጅ ቢል ሰቴፒን በተመሳሳይ ቫይረሱ ተገኝቶበታል።