ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔዘርላንድስ፡ የኔዘርላንድስ ፖሊስ ትልቁ ነው ያለውን የኮኬይን ማምረቻ ማግኘቱን አስታወቀ
የኔዘርላንድስ ፖሊስ በአገሪቱ ታሪክ ትልቁ ነው ያለውን የኮኬይን ማምረቻ ላቦራቶሪ ማግኘቱን አስታወቀ።
ማምረቻው የተገነባው ከዚህ ቀደም የፈረስ ግልቢያ ማስተማርያ በነበረ ስፍራ ላይ ነው ተብሏል።
ፖሊስ አካባቢውን የተቆጣጠረው ባለፈው አርብ ሲሆን የማምረቻ ላብራቶሪው የሚገኘው በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ገጠራማ አካባቢ ነው።
በማምረቻ ስፍራው ነበሩ 17 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል።
"ይህ በኔዘርላንድስ እስከዛሬ ድረስ ከተገኙት ማምረቻዎች ሁሉ ትልቁ ነው" ያሉት የፖሊስ ኃላፊው አንድሬ ቫን ሪጂን ሲሆኑ፤ አክለውም በቀን ከ150 እስከ 200 ኪሎ ግራም ድረስ እፅ የማምረት አቅም እንዳለው አስታውቀዋል።
ይሀን ያህል መጠን ያለው ኮኬይን ወደ 5.3 ሚሊየን ዶላር ዋጋ እንደሚያወጣም የፖሊስ ኃላፊው ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ማክሰኞ ዕለት የወጣው የፖሊስ መግለጫ እንደሚያስረዳው ግምቱ የተሰራው በስፍራው ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ብዛት፣ የማምረቻ መሳሪያዎቹ ዓይነትና ተከላ፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ገብተው ነው ይላል።
ከማምረቻ ቁሳቁሶቹ ባሻገር በሺዎች ሊትር የሚቆጠሩ ኬሚካሎች እንዲሁም 100 ኪሎ ግራም ኮኬይን በማምረቻ ስፍራው መያዙን አስታውቀዋል።
ፖሊስ በተጨማሪም 120 ቶን የሚመዝን "የማጓጓዣ ቁሳቁስ" በአፔልዶሮን ከተማ መያዙን አስታውቋል።
እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ይህ የማጓጓዣ ቁሳቁስ በብዛት ልብስ ሲሆን በኮኬይን እንዲሞላና እንዲለበጥ ከተደረገ በኋላ ወደ ሚፈለገው ስፍራ በማጓጓዝ በኬሚካል እንዲራገፍ ይደረጋል ተብሏል።
ፖሊስ 16 ተጠርጣሪዎችን ከዚህ ቀደም የፈረስ ግልቢያ ማስተማሪያ በነበረው ስፍራ በቁጥጥር ስር ሲያውል፣ አንዱ ደግሞ የመጋለቢያው ባለቤት የነበረ ግለሰብ በአልፔድሮን መያዙ ተገልጿል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት አብዛኞቹ ግለሰቦች የኮሎምቢያ ፓስፖርት ያዙ መሆናቸውም ተገልጿል።
በዚህ ሳምንት ረቡዕ እና ሐሙስ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሏል።