ቻይና በአደንዛዥ ዕፅ ክስ ሁለተኛ የካናዳ ዜጋ ላይ የሞት ፍርድ በየነች

ዕጽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቻይናው ፍርድ ቤት አደንዛዥ ዕፅ ማምረት በሚል ክስ ሁለተኛ የካናዳ ዜጋ ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈ።

በጉዓንዶንግ ግዛት የሚገኘው ፍርድ ቤት የካናዳ ዜጋ በሆነው ዬ ጂዓንሁኢ ላይ የሞት ፍርድ ማስተላለፉን ትናንት አስታውቋል።

ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ሌላ የቻይና ፍርድ ቤት በተመሳሳይ የካናዳ ዜጋ በሆነው ዡ ዌይሆንግ ላይ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ ክስ የሞት ፍርድ አስተላልፏል።

ግለሰቦቹ በቻይና በቅርቡ የሞት ፍርድ የተበየነባቸው 3ኛ እና 4ኛ የካናዳ ዜጎች ሆነው ተመዝገበዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ የሁዋዌ ሥራ አስፈጻሚ በካናዳዋ ቫንኩቨር ከተማ በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ በቻይና እና ካናዳ መካከል ያለው ግነኙነት ወጥረት ሰፍኖበታል።

የሁዋዌዋ ሥራ አስፈጻሚ ሜንግ ዋንዛሁ በካናዳ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለችው ከአሜሪካ ለካናዳ በቀረበ ጥያቄ ነበር።

ከዚህ ቀደምም በአውሮፓውያኑ 2018 ማገባደጃ ላይ የቻይና ባለስልጣናት ለውጪ አገር ሲሰልሉ ነበሩ ያሏቸውን ሁለት የካናዳ ዜጎች በቁጥጥር ሥር አውለው ነበር።

የቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ግን በካናዳ ዜጎች ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ ከቻይና-ካናዳ ግነኙነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብለዋል።

ትናንት የሞት ፍርድ የተላለፈበት ዩ ጂዓንሁኢ የክስ ዝርዝር ይፋ ባይደረግም፤ የቻይና መገናኛ ብዙሃን ግን ዩ እና ሌሎች 5 ቻይናውያን ከሚጠቀሙበት ክፍል ውስጥ ፖሊስ 218 ኪ.ግ የሚመዝን ኤክስታሲ የተባለ ዕፅ ማግኘቱን ዘግበዋል።

ከአምስቱ ቻይናውያን መካከል አንዱ የሞት ፍርድ የተላለፈበት ሲሆን የተቀሩት ከ7 ዓመት እስከ የእድሜ ልክ እስራት እንደተበየነባቸው ተንግሯል።

ሌላኛው ሐሙስ ዕለት የሞት ፍርድ የተላለፈበት የካናዳ ዜጋ ዡ ዌይሆንግ ኬታማይን የተሰኘ ዕፅ በማምረት ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው ተብሏል።