በኔዘርላንድ 'የዓለም ፍፃሜ'ን በምድር ቤት ተደብቆ ሲጠባበቅ የነበረው ቤተሰብ ተገኘ

በኔዘርላንድስ ሪዩኔርዎልድ አባት እና ስድስት ልጆች ይኖሩበት የነበረው የእርሻ አካባቢ የሚያሳይ የድሮን ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ ስውር የሆነውን ቤት ፈልጎ ካገኘው በኋላ "ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ" ብሏል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኔዘርላንድስ ለዘጠኝ ዓመታት ምድር ቤት ባለ ክፍል ውስጥ ሆነው የዓለምን ፍፃሜ ሲጠባበቁ የነበሩ የቤተሰብ አባላት በፖሊስ መገኘታቸውን ሪፖርቶች አመለከቱ። ፖሊስ ሥፍራውን ሊያገኘው የቻለው ከቤተሰቡ መካከል አንደኛው መጠጥ ቤት መታየቱን ተከትሎ ነው።

የ58 ዓመቱ ጎልማሳና እድሜያቸው ከ18 እስከ 25 የሚደርሱ ወጣቶች በኔዘርላንድስ ድሬንዝ ግዛት ይኖሩ ነበር።

በምስጢር ከሚኖሩበት ቤት ሊገኙ የቻሉትም ከልጆቹ በእድሜ ከፍ የሚለው ግለሰብ በሩዩኔርዎለድ መንደር አቅራቢያ ወደ አንድ መጠጥ ቤት ጎራ ብሎ መጠጥ ሲያዝ በመታየቱ ነበር።

ከዚያም የመጠጥ ቤቱን ሠራተኞች እርዳታ እንደሚፈልግ መጠየቁን አር ቲ ቪ ድሬንዝ ዘግቧል።

ለቤተሰቡ አባት ይሆናል ተብሎ ተገምቶ የነበረው ጎልማሳ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፤ የአካባቢው ከንቲባ "እንደዚህ ዓይነት ነገር አይቼ አላውቅም" ሲሉ ጉዳዩ የተለየ እንደሆነ አስረድተዋል- ኖር የእርሻ ቦታው ባለቤት እንደነበሩ በማከል።

አንድ የዜና ማሠራጫ እንዳለው ቤተሰቡ ከአካባቢው ማህበረሰብ ራሳቸውን አግልለው 'የዓለም ፍፃሜን' እየተጠባበቁ ነበር። የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም ከተገኙት መካከል የልጆቹ አባት ይገኙበታል ተብሏል።

የመጠጥ ቤቱ ባለቤት ክሪስ ዌስተርቢክ ግለሰቡ እንዴት ወደ መጠጥ ቤቱ እንደመጣና አምስት ቢራዎችን አዝዞ እንደጠጣ አስረድተዋል።

"ሳወራው ነበር፤ ከዚያም ከተናገረ በኋላ ማምለጥ እንደሚፈልግ ጠየቀ፤ ወዲያውኑ ፖሊስ ጋ ደወልን" ብሏል።

አክለውም "ረጅም ፀጉር፣ የቆሸሸ ጢም ነበረው። አሮጌ ልብሶችን ለብሶ ሲታይ ግራ እንደገባው ያስታውቅ ነበር፤ ትምህርት ቤት ገብቶ እንደማያውቅ እና ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ወደ መጠጥ ቤት ጎራ ብሎ እንደማያውቅም ያወራ ነበር" ብለዋል።

ግለሰቡ ወንድምና እህቶች እንዳሉትና በአንድ የእርሻ አካባቢ እንደሚኖሩ ተናግሯል። እርሱ ታላቅ በመሆኑም የእህትና ወንድሞቹን አኗኗር መለወጥ ይፈልግ እንደነበር ለመጠጥ ቤቱ ባለቤት አጫውቷቸዋል።

ፖሊስ ባደረገው አሰሳ የእርሻ መንደሩ አካባቢ የሚገኘውን መኖሪያ ቤት የጎበኘ ሲሆን በሳሎኑ ውስጥ፤ የተከለለ እና ቤተሰቡ ተደብቀውበት ወደ ነበረው ምድር ቤት የሚወስድ የመወጣጫ ደረጃ እንደተመለከተ ገልጿል።

ሩኔርዎልድ ከ3 ሺህ የሚያንሱ ሰዎች የሚኖሩባት ትንሽ መንደር ናት። የእርሻ ቦታው ከመንደሩ ወጣ ብሎ የሚገኝ ሲሆን ከከተማው ጋር በአንድ ወንዝ ላይ በተገነባ ድልድይ ይገናኛል።

በከፊል በዛፎች የተደበቀው የእርሻ ቦታ የአትክልት ማምረቻ ሰፊ ቦታ ያለው ነው፤ ፍየሎችም ይረቡበታል።

አንድ ጎረቤት ለደች ሚዲያ እንደተናገሩት ሁል ጊዜ በእርሻው አቅራቢያ ልጆች የሌሉት አንድ ሰው ብቻ እንደሚመለከቱና እንስሳት [ዝይ እና ውሻ] እንደነበሩት ገልፀዋል።

የአካባቢው ፖስተኛ በበኩሉ አንድም ቀን ቢሆን ወደ ቤቱ ደብዳቤ አድርሶ እንደማያውቅ አስረድቷል። " የሚያምርና አስፈሪ የሆነ ነገር ነው፤ አሁን ነው ማሰብ የቻልኩት" ሲል ለአልገሚን ዳግብላድ የዜና ድረ ገፅ ተናግሯል።

በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ዜናውን በትዊተር ገፅ ላይ ያጋሩት ሲሆን አንድ ዘጋቢም "ፎቶግራፉን ሳነሳ ትንሽ እንድርቅ ተጠይቄ ነበር" ሲል የእርሻ ቦታውን ምስል ለጥፎታል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

Presentational white space

የ58 ዓመቱ ጎልማሳ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት እንደሆነ ፖሊስ አረጋግጧል።

"የሆነ ሰው [ እዚያ የነበሩ] በቤቱ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁኔታ አሳስቦናል ሲሉ" በትዊተር ገፃቸው በማስፈራቸው ወደ ሥፍራው እንዳቀኑ ፖሊሱ አክለዋል።

"እስካሁን ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ" የሚለው ፖሊስ ምርመራቸው ግን እንደቀጠለ አስረድተዋል።

ቤተሰቡ ለምን ያህል ጊዜ ምድር ቤቱ ውስጥ እንደቆየና በልጆቹ እናት ላይ ምን እንደተፈጠረ የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ የአካባቢው ከንቲባ ግን ከዓመታት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየች ተናግረዋል።

የ58 ዓመቱ ግለሰብ በስትሮክ ይሰቃይ እንደነበርና አልጋ ላይ ውሎ እንደነበር አንዳንድ ሪፖርቶች አመልክተዋል።