በዴሞክራቲክ ኮንጎ ጀልባ ሰጥሞ 34 ሰዎች ሞቱ

እቃ እና ሰዎች ማመላለሻ ትልቅ ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በዴሞክራቲክ ኮንጎ በኮንጎ ወንዝ ላይ መንገደኞችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ጀልባ ሰጥሞ ቢያንስ 34 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

ፖሊስ እንዳስታወቀው ከአደጋው 76 ተሳፋሪዎች በህይወት መትረፍ የቻሉ ሲሆን በወቅቱ ጀልባው ከአቅሙ በላይ በጣም ብዙ ሰው ሳይጭን እንዳልቀረ ተገምቷል።

ጀልባው ከሃገሪቱ ዋና ከተማ ኪንሻሳ በመነሳት ማይ ንዶምቤ ወደተባለችው ሰሜናዊ ግዛት እየተጓዘ ነበር።

የአደጋው መንስኤ እስካሁን እንዳልታወቀ የገለጸው ፖሊስ ተሳፋሪዎቹ የውሃ ላይ መንሳፈፊያ ጃኬቶችን አድርገው ነበር ብሎ ለማሰብ እጅግ አስቸጋሪ ነው ብሏል።

በዴሞክራቲክ ኮንጎ የውሃ ላይ ጉዞ በጣም የሚዘወተር ሲሆን ጀልባዎች የተለያዩ ጭነቶችና ተሳፋሪዎች ከአቅም በላይ ጨነው ሲጓዙ መመልከት የተለመደ ነው።

እስከ 40 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያላቸውና አንዳንዴም ባለሁለት ክፍል ትልልቅ ጀልባዎች ግልጋሎት ላይ ሲውሉ ይስተዋላል። ሁሉም ተሳፋሪዎች ደግሞ ውሃ ዋና ይችላሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ የአስፋልት መንገዶች በጣም የተበላሹና ከጥቅም ውጪ በመሆናቸው ብዙ የሃገሬው ሰዎች በጀልባ የሚደረጉ ጉዞዎችን ምርጫቸው ያደርጋሉ።