ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢንዶኔዥያ ልትሰጥም የምትችለውን ጃካርታን ሽሽት ዋና ከተማ ልትቀይር ነው
ኢንዶኔዥያ ዋና ከተማዋን ወደ ምስራቅ ካሊማንታን ልታዛውር እንደሆነ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ጆኮ ዊዶዶ አሳውቀዋል።
የወቅቱ ዋና ከተማ ጃካርታ 10 ሚሊዮን ነዋሪዎች ሲኖሯት የከተመችበት መሬት ሊሰጥም ይችላል በሚል ነው ከተማ መቀየር ያስፈለገው።
የከተማዋ የተወሰነ ክፍል በዓመት 25 ሴንቲ ሜትር እየሰጠመ እንዳለ ሲነገር የከተማዋ ግማሽ ክፍል ከባሕር ወለል በታች እንደሚገኝ ይታወቃል።
አዲሷ ዋና ከተማ የትኛዋ ልትሆን እንደምትችል ባይገለፅም ቦሬኖ የተሰኘችው ደሴት ላይ እንደሚሆን ተነግሯል።
በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ስለከተማ ቅየራው ንግግር ያሰሙት ፕሬዝደንት ዊዶዶ "አዲሲቱ ዋና ከተማችን ምቹ ቦታ ላይ ትገነባለች። ለሁሉም አማካይ የሆነ ቦታም ነው። ለሌሎች ከተማዎችም የቀረበ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ጃካርታ የገዢው መንግሥት መቀመጫና የበርካታ መሥሪያ ቤቶች መናኸሪያና የንግድ ማዕከል ናት።
አዲሲቱ ከተማ የመስጠምም ሆነ ሌላ ተፈጥሯዊ አደጋ እንዳማያሰጋት ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው አስረግጠዋል።
አዲሲቱን ከተማ ለመግንባት 32 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሻ የሃገሪቱ ገንዘብ ሚኒስትር አሳውቀዋል። ወጪው የበዛ ነው የሚባል እንዳልሆነም ነው ሚኒስትሩ የሚናገሩት።
የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ዋና ከተማ ሊገነባበት የታሰበበት ቦት በርካታ ብርቅዬ እንስሳት የሚገኙት ቦታ መሆኑን በማንሳት ይቃወማሉ።
ኢንዶኔዥያ ማዕከላዊ መንግሥቷን እንደትበትንና ሥልጣንን ወደ ክልላት እንድታከፋፍል ዋና ከተማ መቀየሯ መፍትሄ ነው ብለው የሚከራከሩም አልጠፉም።
ጃካርታ የምትገኝበት የጃቫ ደሴት ከሌሎች ደሴቶች የተሻለ ተጠቃሚ ነች እየተባለች ስትታማ ቆይታለች።
የደሴቶች ስብሰብ የሆነችው ኢንዶኔዥያ ከ18 ሺህ በላይ ደሴቶች እንዳሏት ይታወቃል።