ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ ተሻገረ
በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሬ ቢያሳይም በተመሳሳይ መልኩ የሚያገገግሙ ሰዎችም እንዲሁ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል። በትናንትናው ዕለት አስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 327 ሰዎች እንዲሁም በዛሬው ዕለት 117 ማገገማቸውንም የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። በዚህም መሰረት እስካሁን በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 2132 ደርሷል። በዛሬው ዕለት አምስት ሰዎች መሞታቸውንም ተከትሎ ሃገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 98 አድርሶታል። ሃገሪቱ በመቶዎች የመመርመር አቅሟን ጨምሮ በቀን ውስጥ በሺዎች የላብራቶሪ ምርመራዎችን ማከናወን ችላለች። እስካሁንም 246 ሺህ 911 የላብራቶሪ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን በአጠቃላይ 5 ሺህ 679 በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
የቀጥታ ሽፋን
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 119 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ
ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 3895 የላብራቶሪ ምርመራ 119 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በሃገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5689 ደርሷል።
ከዚህም በተጨማሪ በዛሬው ዕለት የአራት ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን ሃገሪቱ በኮሮናቫይረስ ያጣቻቸውን ዜጎች ቁጥር 98 አድርሶታል።
ከሞቱት ውስጥ ሶስቱ በጤና ተቋም ላይ በህክምና ላይ የነበሩ ሲሆን አንደኛዋ ደግሞ በአስከሬን ላይ በተወሰደ ናሙና መሆኑንም የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እለታዊ መግለጫ ጠቁሟል።
በትናንትናው ዕለትም 117 ሰዎች፤ 78 ከአዲስ አበባ፣ 35 ከትግራይ ክልልና 4 ከድሬዳዋ ማገገማቸውን ተከትሎ በአጠቃላይ በሃገሪቱ ያገገሙ ሰዎችን ቁጥር 2132 አድርሶታል።
በዩናይትድ ኪንግደም የ95 ዓመቷ የእድሜ ባለጸጋ ከኮሮና አገገሙ
በዩናይትድ ኪንግደም ሜጋን ዊሊያምስ የተባሉ የ95 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ከኮቪድ-19 ማገገማቸው ተሰምቷል፡፡
ሜጋን ሰባት ሳምንታትን ከኮሮና ጋር እየታገሉ በሆስፒታል ካሳለፉ በኋላ አገግመው ማልትሪዝ ወደሚገኘው የእንክብካቤ ማዕከላቸው ተሸኝተዋል፡፡
ከሆስፒታል ሲወጡም የሆስፒታሉ ሰራተኞች የተሰናበቷቸው በጭብጨባ ነበር፡፡
ሴት ልጃቸው ሜር ሊይንች ከመጋቢት ወር መጀመሪያ አንስቶ እናቷን አለማየት ከባድ እንደነበር ገልጻ፤ ከበሽታው ማገገማቸው ግን እፎይታን እንደሰጣት ተናግራለች፡፡
የልጅ ልጃቸው ጆን ግሪፊዝ በበኩሉ አያቱ ጠንካራ በመሆናቸው የተደረገላቸው አቀባበልና አሸኛኘት ሁሉ ይገባቸዋል ብሏል፡፡
በቫይረሱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ያጣችው ኢራን ማስክ ማድረግን አስገዳጅ ልታደርግ ነው
ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት በቫይረሱ ክፉኛ የተመታችው ኢራን ከሚቀጥለው እሁድ ጀምሮ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረግን አስገዳጅ እንደምታደርግ አስታወቀች፡፡
ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሀኒ ለአገሪቷ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ ሕጉን በተላለፉ ላይ ስለሚከተለው ቅጣት ያሉት ነገር የለም፡፡
እንደ ምክትል የጤና ሚኒስትር ከሆነ ግን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ እንደ ግብይት ቦታዎች እና የመንግሥት ተቋማት ያሉ የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዙባቸው ቦታዎች የሚሄዱ ሰዎች አገልግሎት አያገኙም፡፡
ፕሬዚዳንት ሩሃኒ አክለውም የቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋባቸው ባሉ አካባቢዎች ገደቦች እንደገና ሊጣሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በኢራን እስካሁን ቢያንስ 222 ሺህ 669 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 10 ሺህ 508 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል፡፡
በእስያ አገራት ምን አዲስ ነገር ተሰማ? ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን . . .
በእስያ አህጉር ከተሰሙ ወረርሽኙን የተመለከቱ አበይት መረጃዎች መካከል፡-
- ቻይና፡ ቻይና እንደ አዲስ ያገረሸውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በቤጂንግ አቅራቢያ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች፡፡ በዚህም ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ወደ አንክሰን ግዛት እንዳይገቡም ሆነ እንዳይወጡ ይገደዳሉ፡፡
- ደቡብ ኮሪያ፡ ምንም እንኳን የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር እየታገለች ቢሆንም ባለፉት 24 ሰዓታት በርካታ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች፡፡ አገሪቷ ባለፈው ወር የአካላዊ ርቀትን ሕግ ካላላች በኋላ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡
- ጃፓን፡ በዋና መዲናዋ ቶክዮ እሁድ ዕለት 60 አዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም ባለፈው ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ካነሳች በኋላ የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል፡፡
- ሕንድ፡ በሕንድ ደልሂ ክፉኛ በቫይረሱ የተጠቃች አካባቢ ስትሆን እስካሁን 73 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተነግሯል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ክትትል የማድረጉ ሥራ ደካማ መሆኑ፣ በአገሪቷ የተንሰራፋው ቢሮክራሲ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች ቁጥሩ እንዲያሻቅብ አድርጎታል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 3636 ደረሰ
በአዲስ አበባ በትናንትናው ዕለት 94 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ በከተማዋ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 3636 አድርሶታል።
በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የቀዳሚ ስፍራነትን የያዘች ሲሆን እስካሁንም ድረስ 789 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፣ በመቀጠልም በቦሌ 504 እንዲሁም በጉለሌ 417 ሰዎች መያዛቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ መግለጫ መረዳት ተችሏል።
መግለጫው ጨምሮም በትናንትናው ዕለትም የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉንም አሳውቋል።
317 የከተማ ነዋሪዎች ደግሞ ከህመሙ ማገገማቸው ተገልጿል።
በአለም ላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአስር ሚሊዮን በላይ ሆነ
በአለም ላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአስር ሚሊዮን መብለጡን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዪኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 499 ሺህ 124 መድረሱ የተገለፀ ሲሆን፤ በጥቂት ሰዓታትም ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ይደርሳል ተብሏል።
በህንዷ መዲና ደልሂ የቤት መቀመጥ መመሪያው "ፍሬ አልባ" ነበር ተባለ
የህንዷ መዲና ደልሂ አስገዳጅ የቤት መቀመጥ አዋጅ ብታስተላልፍም የኮሮናቫይረስ የስርጭት ማዕከል ሆናለች።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 77 ሺህ መድረሱም ተገልጿል።
ለባለፉት ሁለት ወራት ያህል ሃገራዊ አስገዳጅ የቤት ውስጥ ማስቀመጥ አዋጅ ቢተላለፍም የከተማው አስተዳደር በአግባቡ አልተጠቀመበትም ተብሏል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዲሁም የታወቀ ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ክትትል የማድረጉ ስራ በጣም ደካማ እንደነበር ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በሃገሪቱ የተንሰራፋው ቢሮክራሲ፣ ከግል ጤና ማዕከላት ጋር የነበረው ትብብር ደካማ መሆን እንዲሁም ሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለቁጥሩ መጨመር የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸውም እየተነገረ ነው።
ከደልሂ በተሻለ መልኩም ሌሎች የህንድ ከተሞች በተሻለ መጠን የቫይረሱን መዛመት ተቆጣጥረውታል። የደቡባዊቷ ከተማ ባንጋሎር በቫይረሱ ከተያዙ ህሙማን ጋር ግንኙነት እንዲሁም የታወቀ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ክትትል አድርጎ በመመርመርም አድናቆት ተችሯታል። በዚህም የቫይረሱን ስርጭት መግታት ችላለችም ተብሏል።
በቼናይ በተባለችውም ግዛት እንዲሁ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በተሰራው ስራ የሟቾችን ቁጥር መቀነስ እንደተቻለም ተገልጿል።
ሲሪላንካ ለወራት ጥላው የነበረውን የሰዓት እላፊ አነሳች
ሲሪላንካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር መጋቢት ወር ላይ ጥላው የነበረውን የሰዓት እላፊ አዋጅ ሙሉ በሙሉ መነሳቱን አስታውቃለች፡፡
የአገሪቷ ባለሥልጣናት ቀስ በቀስ በቀን የተጣለውን የሰዓት እላፊ ቢያነሱም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ለአራት ሰዓታት የሚቆዩ ጥብቅ ገደቦች ግን እንዲቆዩ አድርገው ነበር፡፡
ምንም እንኳን የሰዓት እላፊው ቢነሳም ሰዎች አሁንም ጥንቃቄ እንዳይለያቸው የጤና ባለሥልጣናት አሳስበዋል፡፡
ከሌሎች ደቡብ እስያ አገራት ጋር ሲነጻጸር ሲሪላንካ የጣለችው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብና ያካሄደችው ሰፊ ምርመራ የሞት ቁጥሩን ለመቀነስ ረድቷታል፡፡
በአውስትራሊያ የቫይረሱ ሥርጭት የጨመረው በ'ሲጋራ መለኮሻ (ላይተር)' ሰበብ እንደሆነ ተገለፀ
አውስትራሊያ ምንም እንኳን በሌሎች ግዛቶች ቫይረሱን እየተቆጣጠረች ቢሆንም በቪክቶሪያ ግዛት ግን አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡
የግዛቷ አስተዳዳሪ ዳንኤል አንድሪውስ፤ የተቀሰቀሰው ወረርሽኝ የአንድ ሆቴል ሰራተኞች የሲጋራ መለኮሻ (ላይተር) በመጋራታቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ተናግረዋል፡፡
አስተዳዳሪው በሰጡት መግለጫ "ሰራተኞቹ አካላዊ ርቀታቸውን ቢጠብቁም መለኮሻውን ግን እርስ በርስ ሲቀባበሉ ነበር" ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ሰራተኞቹ እንደሚፈለገው አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ በአንድ ላይ በመኪና ተጉዘው ነበር ሲሉ አክለዋል፡፡
ቪክቶሪያ ከባህርዳርቻ ጉዞ የሚመለሱ ሰዎች ምርመራ ማድረግ አስገዳጅ እያደረገች እንደሆነ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በግዛቷ እሁድ ዕለት ብቻ 49 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከሁለት ወር በበለጠ ጊዜ ውስጥ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል፡፡
በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሆነ
በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊየን በላይ የደረሰ ሲሆን በፍሎሪዳና ቴክሳስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቧል፡፡
በአገሪቷ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙት ግዛቶች የወረርሽኙ ሥርጭት የጨመረው በቅርብ ሳምንታት የንግድ ተቋማት እንዲከፈቱ ከተፈቀደ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
ቅዳሜ ዕለት በፍሎሪዳ ከ9ሺህ 500 በላይ አዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ አርብ ዕለት ከተመዘገበው በ500 ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የግዛቷ ባለሥልጣናት በንግድ ተቋማት ላይ ጥለውት የነበረውን ገደብ ሊያጠብቁ ነው፡፡
ቴክሳስ ከአርብ ዕለት ጀምራ ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች፡፡
የአሜሪካ መንግሥት የኮሮናቫይረስ አማካሪ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ባለፈው ሳምንት "አገሪቷ ከፍተኛ ችግር ነበረባት" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ፋውቺ ለዋይት ሃውስ የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል መግለጫ ላይ እንደተናገሩት "አሁን አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ምክንያት ግዛቶች የጣሏቸውን ገደቦች በመጠኑም ቢሆን ፈጥነው ማላላት ስለጀመሩና ሰዎችም መመሪያዎችን ባለመከተላቸው ሊሆን ይችላል" ብለዋል፡፡
በፍሎሪዳ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ132 ሺህ በላይ ሲሆን ከ3ሺህ 300 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
በዓለማችን በሌሎች አገራት ከተመዘገበው በበለጠ በአገሪቷ ከ125 ሺህ በላይ የኮቪድ -19 ታማሚዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡
በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ከ ሁለት ሺህ ተሻገረ
በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሬ ቢያሳይም በተመሳሳይ መልኩ የሚያገገግሙ ሰዎችም እንዲሁ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል።
በትናንትናው ዕለት አስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 327 ሰዎች ማገገማቸውንም የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል።
በዚህም መሰረት እስካሁን በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 2015 ደርሷል። በትናንትናው ዕለት አምስት ሰዎች መሞታቸውንም ተከትሎ ሃገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 94 አድርሶታል።
ሃገሪቱ በመቶዎች የመመርመር አቅሟን ጨምሮ በቀን ውስጥ በሺዎች የላብራቶሪ ምርመራዎችን ማከናወን ችላለች። እስካሁንም 243 ሺህ 016 የላብራቶሪ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን በአጠቃላይ 5 ሺህ 570 በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር ተመዘገበ
በኢትዮጵያ በአንድ ቀን አስካሁን ከተረመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሲሆን ተጨማሪ 145 ሰዎች ላይ ደግሞ ቫይረሱ ተገኝቷል።
አገሪቱ በምታወጣው ዕለታዊ መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል ተጨማሪ 327 ሰዎች ከበሽታው በማገገማቸው እስካሁን በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 2015 አድርሶታል።
ባለፉት 24 ሰዓታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተሰባሰቡ 5 ሺህ 552 ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 145 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ተገለጸ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ የወረርሽኙ ሁኔታ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 59ኙ ሴቶች ሲሆኑ 86ቱ ወንዶች ናቸው።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 94 ከአዲስ አበባ፣ 22 ከኦሮሚያ፣ 10 ሶማሌ፣ 10 አማራ፣ 6 ድሬዳዋ እና 3 ከቤኒሻንጉል ክልሎች ናቸው።
በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥርም በ5 የጨመረ ሲሆን በዚህም በአገሪቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 94 ደርሷል።
በኢትዮጵያ እስካሁን 243 ሺህ 016 ናሙናዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በአጠቃላይ 5 ሺህ 570 ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች አግኝታለች።
68 ቀናት ፅኑ ሕሙማን ክፍል የከረመው የኮቪድ-19 ታማሚ
ኢትዮጵያ፡ ከ230 ሺህ በላይ ሰዎች ተመርምረው ከ5400 በላይ ህሙማን ተገኝተዋል
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ በነበሩት አራት ወራት ውስጥ እስካሁን ለ237 ሺህ 464 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ በ5425 ሰዎች ላይ ተገኝቷል።
ከእነዚህም መካከል 1688 ሰዎች ባለፉት ወራት ውስጥ በተደረገላቸው ህክምና ከወረርሽኙ አገግመዋል። ከበሽታው ጋር በተያያዘም አስካሁን 89 ሰዎች መሞታቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ያወጡት መረጃ ያመለክታል።
አስካሁን በተደረገው ምርምራ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን የተገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደሆነ የከተማዋ ጤና ቢሮ የሚያወጣው መረጃ ያመልከታል።
በዚህም መሰረት በአገሪቱ በሽታው ከተገኘባቸው 5425 ሰዎች መካከል 3545 ሰዎች አድራሻቸው አዲስ አበባ ውስጥ ነው ተብሏል።
የኬንያ አየር መንገድ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ እንደሚገጥመው ገለጸ
ሥራው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተስተጓጎለበት የኬንያው አየር መንገድ በዚህ ዓመት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ ሊያጋጥመው እንደሚችል ተገለጸ።
በዚህ ምክንያትም አየር መንገዱ በሥራው ለመቀጠል የሚያስችለውን የ70 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ከመንግሥት ለማግኘት ከመጠየቅ በተጨማሪ ሠራተኞችን መቀነስና ዋና ዋና ንብረቶቹን መሸጥን ጨምሮ ከባድ ውሳኔዎችን ሊወስን እንደሚችል እየተነገረ ነው።
የኬንያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለን ኪላቩካ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ድርጅቱ ትኩረቱን ከመንገደኞችና ከጭነት አገልግሎት በተጨማሪ ወደ ሌሎች ዘርፎች እንዲያሰፋ የሚያስችለው ዕቅድ ላይ እየሰራ ሲሆን፤ መልሶ የማዋቀር ተግባርም የአየር መንገዱን ቦርድ ውሳኔን እየጠበቀ ነው።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የኬንያ አየር መንገድ በከፍተኛ የሥራ ማስኬጃ ወጪ ምክንያት የተጣራ 122 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሞት ነበር።
የጸረ ወባ መድኃኒት እጥረት እያጋጠመ ነው
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ የወባ በሽታ መድኃኒት ሃይድሮክሲክሎሮከዊን በሽታውን ለመከላከልና ህሙማንን ለማከም በሚል መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ጸረ ወባ የሆነው ይህ ሃይድሮክሲክሎሮከዊን የተባለው መድኃኒትን ለኮሮናቫይረስ ህክምና እንዲውል የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ጃይር ቦልሶናሮ እና የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ሲቀሰቅሱ ነበር። ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንዲያውም በሽታውን ለመከላከል መድኃኒቱን ለተወሰ ጊዜ መውሰዳቸውን ሲናገሩ ነበር።
በዚህም ሳቢያ ለመድኃኒቱ ያለው ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ በአቅርቦት ላይ እጥረት ሲያስከትል የዋጋ ጭማሪም ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ መድኃኒቱን ለተለያዩ ህክምናዎች በሚወስዱ ህሙማን ላይ ቀጥተኛ ጫናን ማስከተሉ ተነግሯል።
በቅርቡ በሃይድሮክሲክሎሮከዊን ላይ የተደረገ ሙከራ መድኃኒቱ ኮሮናቫይረስን ለማከም አስተዋጽኦ እንደሌለው ቢያመለክትም፤ አንዳንድ አገራት ግን መድኃኒቱ ጥቅም እንዳለው ማስተዋወቃቸውን ቀጥለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትም ሃይድሮክሲክሎሮከዊን ለኮቪድ-19 ህሙማን የሚፈይደው ነገር የለም በማለት በመድኃኒቱ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ሙከራ ማቆሙን ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።
"በአጼ ምኒልክ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበርኩ" ከኮሮናቫይረስ ያገገሙት '114 ዓመቱ' አዛውንት
የሊቨርፑል ከተማ ከንቲባ በእግር ኳስ ደጋፊዎች 'ሁከት' ተበሳጭተዋል
የሊቨርፑል ከተማ ከንቲባ ጆ አንደርሰን የከተማው ቡድን የዋንጫ ባለቤት መሆኑን ምክንያት በማድረግ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተቀመጡ ደንቦችን በጣሱ 'አዋኪዎች' መበሳጨታቸውን ገልጸዋል።
ደጋፊዎች ለሁለት ተከታታይ ምሽቶች ሊቨርፑል የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን ማንሳቱን በማስመልከስ ሲጨፍሩ አምሽተዋል።
ፖሊስ እና ፖለቲከኞች፤ ደጋፊዎች ከቤታቸው ሆነው ደስታቸውን እንዲገልፁ እያሳሰቡ ነው።
ከንቲባ አንደርሰን አርብ ምሽት በጋራ ወጥተው መጠጥ እየጠጡ እሳት በማንደድ ደስታቸውን ሲገልፁ በነበሩ ደጋፊዎች 'ተበሳጭቻለሁ' ብለዋል።
የመርሲሳይድ ከተማ ፖሊስ በኮሮናቫይረስ ሕግጋት መሠረት ደጋፊዎቹን ለመበተን ተገዷል።
ሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ የዋንጫ ደስታውን በሚቀጥለው ዓመት ነገሮች ሲረጋጉ ለማክበር ዕቅድ ይዟል።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ትልቅ ስም ያለው ሊቨርፑል የእንግሊዝ ከፍተኛ ሊግ ዋንጫን የወሰደው ከ30 ዓመታት በኋላ ነው።
የህሙማን ቁጥር በመጨመሩ የአሜሪካ ግዛቶች ዕቅዳቸውን እያዘገዩ ነው
በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ በተደረጉ ምርመራዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው የሚገኙ ሰዎች አሃዝ እያሻቀበ በመሆኑ ግዛቶች ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለማላላት የነበራቸውን ዕቅድ መልሰው እንዲያጤኑት እያስገደደ ነው።
ትናንት አርብ በአሜሪካ ውስጥ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የሚያመለክቱ ውጤቶች ወጥተዋል። ይህም አንዳንድ ግዛቶች ማላላት የጀመሯቸውን እገዳዎች ወደ ማጥበቅ እንዲሁም ሌሎቹ ደግሞ የእንቅስቃሴ እገዳዎችን ለማንሳት ያወጡትን ዕቅድ ለጊዜው ባለበት እንዲቆይ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።
በዚህም መሰረት ቴክሳስ፣ ፍሎሪዳ እና አሪዞና ለበርካታ ሳምንታት ተግባራዊ አድርገዋቸው የነበሩ እገዳዎችን በማንሳት ግዛቶቻቸውን ለእንቅስቃሴ ክፍት የማድረግ ዕቅድ ለማዘግየት ወስነዋል።
ቴከስሳስ በግዛቷ ውስጥ ያሉ ሁሉም መጠጥ ቤቶች እንዲዘጉ ያዘዘች ሲሆን፤ የፍሎሪዳ ገዢ ደግሞ ቀደም ሲል ደረጃ በደረጃ ማንሳት የጀመሩትን እገዳ በመተው ወደቀጣዩ ደረጃ የመሸጋገር ዕቅዳቸውን እንዲዘገይ አድርገዋል።
ካሊፎርኒያን፣ ኔቫዳንና ኦክላሆማን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ግዛቶች ውስጥ እየተገባደደ ባለው በዚህ ሳምንት በአንድ ቀን ውስጥ በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተገኝተውባቸዋል።