በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከል አንድ ሰው ሙሉ ለሙሉ መዳኑ ተገለጸ

የዓለም ጤና ድርጅት ትናንት እንዳስታወቀው የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ዋነኛ ተግዳሮት ከሆኑት መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የመከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት አንዱ ነው። ወደ አገራችን ስንመጣ ደግሞ በትናንትናው ዕለት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደተናገሩት መንግሥት የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ያወጣቸው መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ እየተተገበሩ አይደሉም። የቢቢሲ አማርኛ በመንግሥት የሚሰጡ የመከላከያ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንድታደርጉ እያስታወሰ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ የቀጥታ ዘገባውን ያቀርብላችኋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 600 ሺህ ደረሰ

    በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ ስለተያዙ ሰዎች አዲስ አዲስ የወጣ መረጃ እንዳመለከተው አሁን ቁጥሩ ከ600 ሺህ ማለፉን ተነገረ።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በአውሮፓ በወረርሽኙ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ20 ሺህ ማለፉን በበሽታው ዙሪያ ያለውን መረጃ እየተከታተለ የሚያቀርበው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አመልክቷል።

    አሁን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአንድ መቶ ሺህ የጨመረው አሃዙ ግማሽ ሚሊዮን መድረሱ ከተነገረ በሁለት ቀናት ውስጥ ነው።

    በመላው ዓለም በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 100 ሺህ የደረሰው የካቲት 27፣ 200 ሺህ የገባው መጋቢት 09፣ 300 ሺህ የደረሰው መጋቢት 12 እንዲሁም 400 ሺህ የሆነው ደግሞ መጋቢት 15/2012 ዓ.ም እንደሆነ የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ አመልክቷል።

    ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በበሽታውየተያዘባቸው አገራት፡

    • አሜሪካ 104,865ሰዎች

    • ጣሊያን 86,498ሰዎች

    • ቻይና 81,996ሰዎች

    • ስፔን 72,248ሰዎች

    • ጀርመን 53,340ሰዎች

  2. በኒው ዮርክ ከቤት መውጣት ሊያስቀጣ እንደሚችል ተነገረ

    የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ቢል ደ ብላሲዮ እንዳሉት የአስተዳደራቸውን ከቤት ያለመውጣት ትዕዛዝ ችላ ብለው በሳምንቱ ማብቂያ ቀናት ወደ መናፈሻ ቦታዎችና ወደ እምነት ቦታዎች የሚሄዱ ሰዎች 500 ዶላር ሊቀጡ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ።

    የኒው ዮርክ ከተማ በአሜሪካ ውስጥ የኮሮናቫይረስ በሽታ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተስፋፋባቸው ቦታዎች ቀዳሚዋ ስትሆን እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ነዋሪዎቿ ቫይረሱ የተገኝቶባቸዋል፤ 510ሩ ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።

    በከተማዋ የሚገኙ ሆስፒታሎችም ያላቸው የህክምና መስጫ መገልገያዎች በፍጥነት እያለቁባቸው እንደሆንም እየተነገረ ነው።

    ከተማዋ ህክምና ፈልገው ይጎርፋሉ ብላ በስጋት የምትጠብቃቸውን ነዋሪዎቿ ለማስተናገድ አንድ የባሕር ኃይል መርከብም አንድ ሺህ አልጋዎችን አዘጋጅታ ከቨርጂኒያ ወደ ኒው ዮርክ የባሕር ዳርቻ ታቀናለች ተብሏል። .

  3. ምክትል ከንቲባው በአዲስ አበባ እየተዘዋወሩ ስለኮቪድ-19 መልዕክት አስተላለፉ

    የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመከላከል መደረግ ያለበትን ሁሉም እንዲፈጽም መልዕክት አስተላለፉ።

    ምክትል ከንቲባው በቦሌ፣ በመርካቶ፣ ከመገናኛ እስከ ፒያሳ ባሉት አካባቢዎች ላይ ላገኟቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የበሽታውን መከላከለያ መንገዶች ሲያስታውሱ እንደነበር በምስል አስደግፈው በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ አስፍረዋል።

    አክለውም ሕዝቡ ከበሽታው እራሱን በመጠበቅ ያለውን ውስን አቅም በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

  4. የ101 ዓመቱ ጣሊያናዊ አዛውንት ከኮሮናቫይረስ ዳኑ

    በጣሊያን ያለው ዜና ከምስራች ይልቅ መርዶ የበዛበት ነው። ነገር ግን አንዳንዴም ተስፋ የሚሰጥ ወሬ አይጠፋም።

    በጣሊያን ሰሜናዊ ምሥራቅ በምትገኘው ሪሚኒ ከተማ የ101 ዓመቱ ኢጣሊያዊ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ በኋላ አገግመው ሐሙስ ዕለት ከሆስፒታል መውጣታቸው ተዘግቧል።

    እኚህ ግለሰብ ቅጽል ስማቸው አቶ ፒ ሲሆን መዳናቸውን የተናገሩት የሪሚኒ ከተማ ከንቲባ ግሎሪያ ሊሲ "በእውነት የማይታመን" በማለት የአዛውንቱ መዳን "ለወደፊቱ ተስፋ ይሰጣል" ብለዋል።

    አክለውን "አቶ ፒ አሸንፈውታል!" ያልዋቸው ሲሆን "101 እንኳን ሞልቶን የወደፊት እጣችን ገና አልተቋጨም የሚለውን ለማሳየት ቤተሰቦቻቸው ወደ ቤት አምጥተዋቸዋል" ብለዋል።

  5. ለኮሮናቫይረስ ህሙማን አገልግሎት የሚውለው ቬንትሌተር ዋጋ መጨመሩ ተነገረ

    ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ለኮሮናቫይረስ ህሙማን የሚያስፈልገው የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እና የህክምና መገልገያዎች በብዛት ለመግዛት መንግሥታት ባደረጉት ጥረት ሳቢያ ፍላጎቱ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

    ለወትሮው ቻይና ውስጥ የሚመረተው ቬንትሌተር በነጋዴዎች ተገዝቶ ነበር ለፈላጊዎች ሲቀርብ የነበረው።

    የአንድ ቬንትሌተር ዋጋ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፤ ቀደም ሲል 27 ሺህ ዶላር የነበረው ወደ 96 ሺህ ዶላር አሻቅቧል። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የኮሮናቫይረስ በዓለም ዙሪያ መስፋፋት ለመሳሪያው ያለው ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉ ነው።

    የብሪታኒያ መንግሥት አቅራቢዎችን በመተው በእራሱ መሳሪያዎቹን ለመግዛት እየሞከረ መሆኑ ተነግሯል። ለዚህም ምክንያቱ የመሳሪያዎቹን አቅርቦት መጓተት ለማስቀረት ነው ተብሏል

  6. ሰበር, በኬንያ ተጨማሪ ሰባት ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋገጠ

    የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሙታኢ ካግዌ እንዳስታወቁት ሰባት አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ተገኝተዋል።

    ይህም በኬንያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 38 ያደረሰው ሲሆን ከዚህ በፊት አንድ ሰው በቫይረሱ ምክንያት መሞቱ ይታወቃል።

    አንድ ሰው ደግሞ ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ መዳኑ ይታወሳል።

  7. በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ከተያዙ መካከል አንድ ሰው ሙሉ ለሙሉ መዳኑ ተገለጸ

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከነበሩ 16 ሰዎች መካከል አንዱ ሙሉ በሙሉ መዳኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ አመለከተ።

    ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያጋሩት በኢትዮጵያ ያሉ የኮሮናቫይረስ ህሙማንን መረጃ በሚያሳየው ሰሌዳ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ እስካሁን ድረስ 797 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

    ከእነዚህም መካከል 16 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተመዝግቧል።

    በኢትዮጵያ ውስጥ ተመርምረው ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል ሁለቱ ጃፓናዊያን ወደ አገራቸው የሄዱ ሲሆን አንደኛው ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ በማገገሙ በአገሪቱ የሚገኙ በሽታው ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 13 መሆኑን ያመለክታል።

  8. ስናስልና ስናስነጥስ ለሌሎች ጥንቃቄ እናድርግ

    የእጅን ንጽህና በአግባቡ መጠበቅ ከቻልንና ከሰዎች ጋር የሚኖረንን አካላዊ ቅርርብና ንክኪን ማስወገድ ከቻልን ከኮሮናቫይረስ እራሳችንንና ሌሎችን ለመጠበቅ እንችላለን።

    በቻልነው አቅም ባለሙያዎች የሚመክሩንን የጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድ ከቻልን እራሳችንንም ሆነ ቤተሰባችንን ከወረርሽኙ እንታደጋለን።

    ከዚህ በተጨማሪም በምናስልበትና በምናስነጥስበት ወቅት ሁላችንም አፍና አፍንጫችንን መሸፈን ይኖርብናል።

  9. ሰበር, በስፔን በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ5 ሺህ አለፈ

    በስፔን በኮቪድ-19 ምክንያት ባለፉት 24 ሰዓታት 832 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ 5 ሺህ ማለፉ ተገለፀ።

    በአሁን ሰዓት በአጠቃላይ 5,690 የሞቱ ሲሆን 72,248 ሰዎች ደግሞ መያዛቸው ተገልጿል።

    ስፔን ከጣሊያን ቀጥላ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃች አገር ናት።

    በስፔን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ድረስ የተጣለ ሲሆን በዚህም የተነሳ የንግድ ተቋማት ዝግ ሆነዋል፤ የሰዎች እንቅስቃሴም ተገድቧል።

    የአገሪቱ መከላከያ ኃይል ሆስፒታሎች ያለባቸውን መጨናነቅ ለማገዝ የተሰማራ ሲሆን የሕክምና ባለሙያዎች የመከላከያ ቁሶች እጥረት መኖሩን እያማረሩ ይገኛሉ።

  10. ስልካችንን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል እንዴት እናጽዳ?

    ስልክዎን በኪስዎ፣ በቦርሳዎ አንዳንዴም ወደ መፀዳጃ ቤት ሲሄዱ ይዘውት ይሄዳሉ። ምን ያህል ጀርም ስልክዎ ብቻ ተሸክሞ እንደሚገኝ አስበውታል? ኮሮናንስ ስላለመያዙ ምን ያህል እርግጠኛ ነዎት?

    ስልካችንን ለማጽዳት 70 በመቶ አልኮል ያለው ዋይፐር መጠቀም የሚቻል ሲሆን በረኪና ግን አይመከርም። ቀላል ሳሙናና ውሃም ለማጽዳት እንደሚያገለግልም ባለሙያዎች ይመክራሉ።

  11. በደቡብ ኮሪያ በኮቪድ-19 የተያዙ በርካታ ሰዎች ከበሽታው ዳኑ

    በደቡብ ኮሪያ በቫይረሱ ከተያዙ ይልቅ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ በልጦ መገኘቱ ተገለፀ።

    ዛሬ 146 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸው የተገለፀ ሲሆን ይህም በአገሪቱ የተያዙት ሰዎችን ቁጥር 9,478 ያደርሰዋል።

    ከእነዚህ መካከል ግን 4,811 አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸው ተነግሯል።

    ደቡብ ኮሪያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የያዘችበት መንገድ ያስመሰገናት ሲሆን፤ ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች በመለየት፣ በርካታ ሰዎችን በመመርመር እንዲሁም ለይቶ በማቆየት ከበርካታ አገራት የተሻለ መስራቷ ተገልጿል።

  12. የጋናው ፕሬዝዳንት ደሞዛቸውን በኮቪድ-19 ለተያዙ ድሆች ለመስጠት ቃል ገቡ

    የጋናው ፕሬዝዳንት ለአገራቸው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር የጋና ሦስት ከተሞች በከፊል ከእንቅስቃሴ መታገዳቸውን አስታውቀዋል።

    እገዳው ዋና ከተማዋ አክራም በከፊል ዝግ እንደሚያደርጋት የታወቀ ሲሆን ምግብና መድሃኒት ከሚሸጡ እንዲሁም ከሚገዙ ሰዎች በስተቀር መንቀሳቀስ መከልከሉን ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።

    የጋና ፖሊስና የጦር ኃይል የተጣለውን ገደብ የሚያስፈጽሙ ይሆናል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

    አርብ ምሽት በቴሌቪዥን ቀርበው መግለጫ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በኮቪድ-19 ለተጎዱና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ግለሰቦች የሦስት ወር ደሞዛቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

    በጋና 137 በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሲገኙ እስካሁን ድረስ አራት ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ህመም ሞተዋል።

    ከዚህ ባሻገርም በጋና በኮሮና ተይዘው የነበሩ ሁለት ህሙማን መዳናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

  13. የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው የኢንተርኔት መቋረጥ እንዲቆም ጠየቀ

    የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው የኢንተርኔት መቋረጥ እንደሚያሳስበው ገለፀ።

    ለረዥም ጊዜ ኢንተርኔትና ስልክ ማቋረጥ በተለይ ደግሞ እንደ ኮቪድ-19 ያለ ወረርሽኝ ባለበት ሰዓት ስለበሽታው የሚሰጡ መረጃዎችን ዜጎች እንዳያገኙ ያደርጋል በማለት ባለስልጣናት እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃዎችን ለመስጠት እንዲችሉ አገልግሎቶቹ ክፍት እንዲሆኑ ጠይቋል።

    ኮሚሽኑ በድረገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ኢትዮጵያ ከታህሳስ 28/2012 አንስቶ በምዕራብ ኦሮሚያ ከተሞች ከደህንነት እና ፀጥታ ጋር በተገናኘ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መቋረጡን በመግለጽ፤ ይህም በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች መረጃ እንዳያገኙ፣ እንዲሁም ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ማድረጉን ገልጿል።

    መግለጫው ኢንተርኔት የምታቋርጠው ኢትዮጵያ ብቻ አለመሆኗን በመጥቀስ ሁሉም አገራት በፍጥነት ኢንተርኔትና ስልክ ማቋረጣቸውን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

  14. የኮሮናቫይረስ መነሻ የሆነችው የቻይና ከተማ በከፊል ለእንቅስቃሴ ክፍት ሆነች

    የቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ዋና ከተማ ዉሃን በከፊል ለእንቅስቃሴ ክፍት ሆነች።

    ወደ ዉሃን የመጡ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው ለረዥም ጊዜ ያላዩ ሲሆን ከተማዋን ለቀው መውጣት የሚፈቀድላቸው ከሳምንት በኋላ ነው ተብሏል።

    ዉሃን ከ50 ሺህ በላይ ኮሮናቫይረስ ያለባቸው ሰዎች የተገኙባት ሲሆን 3 ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

    ቻይና በአሁኑ ሰዓት ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ህሙማንን ለመከላከል በሚል የመኖሪያ ፈቃድም ሆነ ቪዛ የያላቸው መንገደኞች ቢሆኑ እንኳ ከአገር ውጪ የሚመጡ የውጪ አገር ዜጎች እንዳይገቡ አግዳለች።

    ዝርዝሩን ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ የቻይናዋ ዉሃን ከተማ በከፊል ለእንቅስቃሴ ክፍት ሆነች

  15. ለኮሮናቫይረስ እየተዘጋጀ ያለው መድሃኒት ወደ ቀጣይ ፍተሻ ማለፉ ተነገረ

    የኮሮናቫይረስን ለማከም የሚያስችል መድሃኒት ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሞዴሊንግ መሰረታዊ የምርምር ሂደትን በስኬት ማለፉን የሳይንስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር አስታወቀ።

    ሚኒስቴሩ መድሃኒቱን በተመለከተ በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት አማካይነት ትናንት የወጣው መረጃ ላይ የተፈጠሩ ያላቸውን "ብዥታዎች" ለማብራራት ዛሬ ባወጠው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ሂደቱ በሳይንሳዊ ምርምር የተደገፈ አገር በቀል እውቀት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር የተቀናጀ ሥራ ነው ብሏል።

    ምርምሩ የተጀመረው የኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ አንስቶ መሆኑን በማመልከት፤ ሥራው በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ሲካሄድ የቆየ እንደሆነ አመልክቷል።

    በዚህም መሰረት መድሃኒቱ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ምርምር ሂደትን አልፎ በቀጣይ በእንስሳት ላይና ክሊኒካል ፍተሻ ወደ ማድረግ ሥራ እንዲሸጋገር ተደርጓል ብሏል፤ ሚኒስቴሩ።

    ጨምሮም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ከባህል ሃኪሞችና ከህክምና ተመራማሪዎች ጋር በመሆን የኮሮናቫይረስን ( ኮቪድ -19) ለማከም የሚያስችል መርዛማነት የሌለውና አዋጭነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት ጥቅም ላይ ለማዋል በመስራት ላይ እንደሚገኙ አብራርቷል።

    ይህንን በተመለከተ በትናንትናው ዕለት የወጣው ዜና መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ በርካታ ጥያቄዎችና ትችቶችም ከተለያዩ ወገኖች በመሰንዘሩ ነው ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ተጨማሪ ማንራሪያ ለመስጠት የተገደደው።

    ሚኒስቴሩ ሲያጠቃልልም የምርምሩን ሂደት በተመለከተ ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችን በቀጣይ እንደሚገልጽ አሳውቋል።

  16. በአዲስ አበባ 41 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ በጸረ ተዋህሲያን መድሃኒት ሊረጭ ነው

    ነገ እሁድ መጋቢት 20 የአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች የፀረ ተዋህሲያን መድሃኒት ይረጫሉ ተባለ።

    መድሃኒት መርጨቱ የሚካሄደው በአዲስ አበባ በሚገኙ 13 ዋና ዋና መንገዶች ላይ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

    በዚህ መሠረት ከመስቀል አደባባይ ተነስቶ ቦሌ፣ ጦር ኃይሎች፣ 4 ኪሎ፣ 6 ኪሎ፣ ከጎተራ እስከ ሳሪስ፣ መገናኛ፣ እንዲሁም የምኒልክ አደባባይ፣ አምባሳደር፣ መስቀል አደባባይ፣ ፓስተር፣ መገናኛ፣ አውቶብስ ተራ።

    እንዲሁም ከተክለሃይማኖት እስከ ብሔራዊ እንዲሁም ሜክሲኮ፣ ካዛንችስና ኡራዔል ያሉት መንገዶች የመድሃኒት እርጭት ይካሄድባቸዋል ተብሏል።

  17. የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሐፊ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸው ተረጋገጠ

    የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሙሳ ፋኪ ማሃማት በኮሮናቫይረስ ስጋት ራሳቸውን ለይተው መቀመጣቸው ትናንት ከተነገረ በኋላ ባደረጉት ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ታወቀ።

    ዋና ጸሃፊው በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት የምርመራ ውጤታቸው ነጻ መሆናቸውን ቢያረጋግጥም በሚታዘዘው መሰረት ለቀጣዮቹ 14 ቀናት እራሳቸውን ለይተው እንደሚቆዩ ገልጸዋል።

    በሽታው የተገኘበት ባልደረባቸውን ያለበት ሁኔታን በተመለከተም በመልካመ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ሙሉ ለሙሉ እንዲሻለው ጸሎታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

    ዋና ጸሐፊ ሙሳ ፋኪ መጀመሪያ ላይ ጥርጣሬ ያደረባቸው የተጠቀሱት ባልደረባቸው በኮቪድ-19 መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።

    በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው የዋና ጸሐፊው ባልደረባ ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታው ከተገኘባቸው 16 ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ሞሪሼሳዊው የ72 ዓመት ሰው መሆናቸው ተጠቅሷል።

    የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሃፊው በመልዕክታቸው ላይ በጸሎታቸው ላሰቧቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበው፤ አፍሪካ ከበሽታው ጋር የምታደርገው ፍልሚያ ገና መጀመሩን በማመልከት ሁሉም በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

  18. ዚምባብዌ ከሰኞ ጀምሮ እንቅስቃሴ ልትገድብ ነው

    የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አገራቸው የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት ከሰኞ ጀምሮ ማንኛውንም እንቅስቃሴ መከልከሏን አስታውቀዋል።

    ዚምባብዌ እስካሁን ድረስ አምስት ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን ስታረጋግጥ አንድ ሰው ደግሞ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሞቷል።

    ለሦስት ሳምንት ዚምባብዌያውያን ቤታቸው እንዲቀመጡ የታዘዘ ሲሆን ምግብና አስፈላጊ የሆነ ሕክምና መሳሪያዎችን ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ከቤት ውጪ ውልፊት ማለት አልተፈቀደም።

    የዚምባብዌ የፀጥታ አካላት ይህንን እንዲያስፈጽሙ መታዘዛቸውም ተገልጿል።

    ይህ የዚምባብዌ ውሳኔ የተሰማው ጎረቤቷ ደቡብ አፍሪካ ለ21 ቀን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ማገዷን ተከትሎ ነው።

    በደቡብ አፍሪካ 1170 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሲኖሩ ሁለት ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸው ይታወቃል።

  19. ሩሲያ የሰዎችን እንቅስቃሴ ማገድ ልትጀምር ነው

    ሩሲያ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት ቭላድሚር ፑቲን "ሥራ የሌለበት ሳምንት" ያሉትን ተግባራዊ ማድረግ ልትጀምር እንደሆነ ተገለጸ።

    በዚህም መንግሥት ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ያስጠነቀቀ ሲሆን ይህ መመሪያ ለሳምንት ሊቆይ ይችላል ብለዋል።

    በሩሲያ ኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር አንድ ሺህ የደረሰ ሲሆን አብዛኞቹ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በሞስኮ ከተማ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል።

    ሩሲያ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ካለው የወረርሽኙ መስፋፋት ጋር ራሷን በማነፃፀር በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የበሽታውን ሁኔታ ወረርሽኝ አይደለም ብላለች።

  20. 150 ቱኒዚያውያን ራሳቸውን በፋብሪካ ውስጥ ዘግተው የፊት መሸፈኛ ጭምብል እያመረቱ ነው

    በቱኒዚያ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩት እነዚህ ሠራተኞች ራሳቸውን በፋብሪካ ውስጥ በመዝጋት በቀን 50 ሺህ የፊት ጭምብል እንዲሁም ሌሎች ለሕክምና ባለሙያዎች የሚያገለግል የመከላከያ ቁሳቁስ በማምረት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

    ሠራተኞቹ በፋብሪካ ውስጥ ራሳቸውን ነጥለው ለሕክምና ባለሙያዎች የሚያገለግሎ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ማምረት ከጀመሩ ሳምንት ሞልቷቸዋል ተብሏል።

    እነዚህ 150 ቱኒዚያውያን የፋብሪካ ሠራተኞች አብዛኛዎቹ ሴቶች ሲሆኑ በፋብሪካ ውስጥ ለአንድ ወር ያህል ዘግተው ሊቀመጡ ወስነዋል።

    የሰሜን አፍሪካዋ አገር ቱኒዚያ እስካሁን ድረስ 227 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ ባለፈው ሳምንት ስድስት ህሙማን መሞታቸው ታውቋል።

    ፋብሪካው ከዋና ከተናዋ ቱኒዝ በደቡባዊ አቅጣጫ ገጠራማ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ከፋብሪካ ሰራተኞቹ ጋር አብረው ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የመድሃኒት ባለመሙያዎችና ምግብ አብሳዮች ይገኙበታል።