"ኮሮናቫይረስን ወጣቶችም ሊቋቋሙት አይችሉም" የዓለም ጤና ድርጅት

በዓለማችን ላይ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 11ሺህ ደርሷል። 250ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ቀደም ብሎ በቻይና የተቀሰቀሰው ይህ ወረርሽኝ፣ አሁን አውሮፓን ማዕከሉ በማድረግ የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት አፍሪካ ለባሰ ቀን እንድትዘጋጅ ያሳሰበ ሲሆን ወጣቶችም ተጋላጭ ናቸው መዘናጋት አይገባም ሲል መልዕክት በትናንትናው ዕለት አስተላልፏል። በአገራችን እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ከወረርሽኙ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በቀጥታ ዘገባችን እናደርሳችኋለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የእስልምና ምክር ቤት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል መደረግ ያለበትን ለእምነቱ ተከታዮች ይፋ አደረገ

    የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማዎች ምክር ቤት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የዕምነቱን ሕግጋት መሰረት ያደረገ ውሳኔ (ፈትዋ) ማስተላለፉን አስታወቀ።

    የዑለማዎች ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የኮሮናቫይረስ ስርጭት አስጊ በመሆኑ ከጁምዓና ከጀመዓ ሶላት መቅረት በሸሪዓው የተፈቀደ በመሆኑ የዕምነቱ ተከታዮች "በቤታቸው ውስጥ መስገድ ይቻላሉ" ብሏል።

    በተጨማሪም በኮሮናቫይረስ የተያዘ ወይም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ለጁምዓም ሆነ ለጀመዓ ሶላት እንዲሁም ለሐይማኖታዊ ትምህርት ወደ መስጂድም ሆነ ሕዝብ ወደሚሰበሰብበት ቦታ መምጣት የተከለከለ መሆኑን አመልክቷል።

    ምክር ቤቱ ሁሉም "ወደ አላህ እንዲመለስና ምህረት እንዲለምን" ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ የጤና ጥበቃ ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የሚሰጡትን ምክርና መመሪያ በመቀበል በሥራ ላይ ማዋል የሁሉም ሐይማኖታዊ ግዴታ እንደሆነ ገልጿል።

  2. ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኮሮናቫይረስ በሽታን ለመከላከል ውሳኔ አሳለፈች

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ያስችላል በማለት የደረሰበትን ውሳኔ በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በኩል አስተላልፏል።

    በዚህም መሰረት ቅዱስ ሲኖዶቹ ቤተ ክርስቲያኗ ጸሎትና ምሕላ አጠናክሮ ከማድረግ በተጨማሪ ጤነኞችን የመጠበቅ፣ ሕሙማን የመንከባከብና የማጽናናት ኃላፊነት አለባት በማለት መደረግ ያለባቸውን ነገሮች አስቀምጧል።

    ከእነዚህም መካከል ከቤተክርስቲያኗ ቀኖና ጋር የማይቃረኑ በሽታውን የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ እንዲደረጉ ያዘዘ ሲሆን፤ ከአነዚህም መካከል አለመጨባበጥ፣ እጅን በሚገባ መታጠብ፣ ሳይጠጋጉ ዘርዘር ብሎ መቆም፣ በሳልና በማስነጠስ ጊዜ መጠንቀቅና በርቀት ሰላምታ መለዋወጥን ምዕመናኑና አባቶች ተግባራዊ እንዲደረጉ ተመክረዋል።

    በተጨማሪም የስብከት ጉባኤዎችና መንፈሳዊ ጉዞዎች ለጥቂት ቀናት እንዲቆሙ፣ በቅዳሴና በምሕላ ጸሎት ጊዜ በቤተ ክርስቲያንና በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምዕመናን ተራርቀው እንዲቆሙ ታዘዋል።

  3. በስፔን የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ነው, በአንድ ቀን 324 ሰዎች ሞቱ

    በስፔን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1,326 ደረሰ። በአንድ ቀን ብቻ 324 ሰዎች መሞታቸውን የተናገሩት የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ትናንትና 235 ሰዎች መሞታቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

    ጤና ሚኒስትሩ አክለውም በአንድ ቀን በቫይረሱ መያዛቸው የተመዘገበ ሰዎች 5ሺህ መሆናቸውን አሳውቀው በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 24,926 መድረሱን ተናግረዋል።

    ስፔን በአሁኑ ሰዓት ከቻይናና ጣሊያን በመቀጠል በአለማችን ክፉኛ በቫይረሱ የተጠቃች ሶስተኛ አገር ሆናለች።

    ከማድሪድ አካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሆስፒታሎች በቫይረሱ በተያዙ ሕሙማን ተጨናንቀዋል።

    የስፔን መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሚል አአንቅስቃሴ ላይ ገደብ የጣለው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር።

  4. ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ እና ራስን አግልሎ መቆየት?, ራስን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ከሚረዱ ነገሮች መካከል ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅና ራስን አግልሎ ማቆየት ይገኙበታል።

    የኮሮናቫይረስ ዓለምን እየናጠ መሆኑን ተከትሎ የትኛውም አገር፤ የትኛውም ቦታ ያለ ሰው ማህበራዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ እንደአስፈላጊነቱም ራሱን ለይቶ ለቀናት እንዲቆይ እየተነገረ ነው።

    ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ወይም ራስን ለይቶ ማቆየት ምን ማለት ነው?

    በእንግሊዝ እድሜያቸው ከ70 በላይ የሆኑ፣ እርጉዝ ሴቶች እንዲሁም ብዙ ጊዜ ለጉንፋን የሚጋለጡ ጎልማሶች ማህበራዊ ርቀትን እንዲጠብቁ በጥብቅ ይመከራሉ።

    ማህበራዊ ርቀት መጠበቅን ተግባራዊ ለማድረግ በተቻለ አቅም ሰዎች ስራቸውን ከቤት መስራት መቻል ይኖርባቸዋል።

    እጅግ አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎችና ስብሰባዎች መደረግ አይኖርባቸውም።

    ከቤት ወጥቶ ጉዞ ማድረግና ተንቀሳቅሶ ከመደብር የፍጆታ እቃዎችን መግዛትም የሚቻል ይሆናል፤ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ሁለት ሜትር ርቀታቸውን ጠብቀው እስከተንቀሳቀሱ ድረስ።

    በተመሳሳይ እጅግ አስፈላጊ ከሆነ ቤተሰብ ጥየቃም ሆነ አቅመ ደካማ ጎረቤቶችን መንከባከብም ይቻላል- ርቀትን ጠብቆ።

    ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን ምንም የቫይረሱ ምልክት የሌለበት ሰው ነው። ምልክት የሚያሳዩ ወይም ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር አብረው የነበሩ ሰዎች ግን ራሳቸውን አግልለው ማቆየት ይኖርባቸዋል።

    ራስን አግልሎ መቆየት ማለት ከቤት አለመውጣት ማለት ሲሆን ወደ ስራ ፣ትምህርት ቤት መሄድ ወይም ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች መገኘት አይፈቀድም።

    ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት እንኳ እንዲወጡ አይመከርም። እነዚህን ነገሮች በውጭ የማቅረብ አገልግሎት እንዲያገኙ ነው የሚመከረው።

    ነገር ግን ይህንንም ማድረግ የማይቻል ከሆነ ከሰዎች ጋር ንክኪ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ወጥቶ መግዛት የግድ ይሆናል።

  5. ለናይሮቢ ከተማ ነዋሪዎች የሙቀት ልኬት እየተካሄደ ነው

    በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ባለስልጣናት ሕዝብ በሚበዛባቸው ሥፍራዎች በመገኘት የሙቀት መለካት እያከናወኑ ነው።

    የናይሮቢ ከተማ የጤና ቢሮ ኃላፊ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች በመገኘት በተመረጡ ሰዎች ላይ የሙቀት ልኬት በማካሄድ እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

    ከተመረጡት ሰዎች መካከል የሙቀት ልኬታቸው ከፍ ያለ እና ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፍለጋቸው የታመነ ዜጎች ወደ ሆስፒታል እንደሚላኩ ጨምረው አስታውቀዋል።

  6. የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ያቋረጠባቸው አገራት ዝርዝር

    ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 አገራት ያደርግ የነበረውን በረራ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ማቆሙን ተናግረው የነበረ ሲሆን አየር መንገዱ ዛሬ የአገራቱን ዝርዝር ያወጣ ሲሆን በረራ የተቋረጠባቸው አገራት ተከታዮቹ ናቸው።

  7. የኮቪድ-19 ምልክቶች ምንድን ናቸው?

    ኮሮናቫይረስ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ሲሆን ሲጀምር በትኩሳት ሲሆን በማስከተልም ደረቅ ሳል ይኖረዋል።

    ከሳምንት በኋላ ደግሞ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል፤ በዚህ ሳቢያም አንዳንድ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የህክምና እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የእነዚህ ምልክቶች መታየት ግን በበሽታው የመያዝ ምልክት ላይሆን ይችላል።

    ምክንያቱም ምልክቶቹ ከተለመዱት የጉንፋንና የኢንፍሉዌንዛ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ ነው።

    ኮሮናቫይረስ የከፋ በሚሆንበት ጊዜ ኒሞኒያን፣ ሳርስን፣ የውስጥ አካላት ሥራ ማቆምን እንዲሁም ሞትን ሊያስከትል ይችላል።

    በዕድሜ የገፉና አስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመምን የመሳሰሉ ቀደም ሲል የነበሩ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች በበሽታው ሲያዙ በጠና የመታመም ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

    ሰዎች በበሽታው ከተያዙ በኋላ ምልክቶችን እስከሚያሳዩ ድረስ እስከ 14 ቀናትን ሊወስድ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል።

    ነገር ግን አንዳንድ አጥኚዎች ምልክት የማየቱ ነገር አስከ 24 ቀናት ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

  8. የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ መልዕክት

    የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የዓለም ጤና ድርጅት ጄነራል ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ያቀረቡትን እጅን የመታጠብ ጥሪ መቀበላቸውን ገልፀው ቀጣዩን መልዕክት አስተላልፈዋል።

    እርስዎስ ራስዎንና በዙሪያዎ ያሉትን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ እያደረጉ ነው?

  9. በአውስትራሊያ 'ስለ ኮሮናቫይረስ አልሰማንም አላየንም' በሚመስል መልኩ ሲዝናኑ የነበሩ በፖሊስ ተበተኑ

    ከቤት ውጪ የሚደረጉ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በገደበችው አውስትራሊያ ፖሊስ ሲድኒ ከተማ ቦንዲ የባህር ዳርቻ 'ስለ ኮሮናቫይረስ አልሰማንም አላየንም' በሚመስል መልኩ ሲዝናኑ የነበሩ ሰዎችን በመበተን የባህር ዳር መዝናኛውን ዘጋ።

    በእነዚህ የባህር ዳር መዝናኛዎች ብዙዎች ዓለም ላይ ምንም ስጋት እንደሌለ በሚመስል መንፈስ ሲዝናኑ የሚያሳዩ ፎቶዎች ትናንት በመገናኛ ብዙሃን፤ በማህበራዊ ሚዲያም ሲዘዋወር ውሏል።

    የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ግሪግ ሀንት የባህር ዳር ተዝናኞቹ ባህሪ ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

    የሚመለከታቸው ህግ አስከባሪ አካላት ማህበራዊ ርቀት መጠበቅን በሚመለከት የተቀመጠው ነገር ተግባራዊነትን ለማረጋገጥ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

    አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከጣለቻቸው እገዳዎች መካከል ከ500 በላይ ሰዎች ስብሰባን ማገድ ነው።

  10. ድምጻዊ አውርለስ ማቤሌ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወቱ አለፈ

    የ67 ዓመቱ አውርለስ ማቤሌ፣ በኮሮና ቫይረስ ምከንያት በፈረንሳይ ሆስፒታል ከገባ በኋላ መሞቱን ቤተሰቦቹ አሳወቁ።

    በበርካታ አፍሪካውያን ዘንድ ሞቅ ባሉና የኮንጎን ባህል በሚያሳዩ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው ማቤሌ ከዚህ በፊትም የጤና ችግር እንደነበረበት የሙያ አጋሮቹ ተናግረዋል።

    ልጁ በፌስቡ ክገጿ ላይ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መሞቱን ተናግራ በሞቱ ልቧ በሐዘን መሰበሩን ገልጻለች።

    ማቤሌ በኮሮናቫይረስ ከተያዘ በኋላ ወደ ሆስፒታል ሐሙስ ዕለት የተወሰደ ሲሆን በዛው ዕለት መሞቱ ተሰምቷል።

  11. የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ርቀትዎን መጠበቅ እንዳለብዎ አይዘንጉ

    ደጋግመው የሰሙት ነገር ቢሆንም አንዴ እናስታውስዎ1

    ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሰዎች እንዲወሰዱ ካስቀመጣቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው።

    ድርጅቱ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች አንድ ሜትር ወይም ሶስት ጫማ እንዲርቁ ያሳስባል።

    ይህ ሰዎች ሲስሉ ወይም ሲያስነጥሱ ከአፍ ወይም ከአንጫቸው የሚወጡ እንጥብጣቢዎች ወደ ሌሎች እንዳይሄድ እንደሚያስችልና ይህም የቫይረሱን መተላለፍ እንደሚያስቀር ተገልጿል።

    እርስዎ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ማሳሰቢያዎችን ተግባራዊ እያደረጉ ነው?

  12. በአሜሪካ የአንድ ቤተሰብ አባላት በኮሮናቫይረስ ምክነያት ሞቱ

    በአሜሪካ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አራት ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሞቱ። የዚህ ቤተሰብ ሶስት አባላትም በቫይረሱ ተይዘው ሆስፒታል ተኝተዋል ተብሏል።

    የ73 አመቷ ግሬስ ፉስኮ በኒውጀርሲ የምትኖር ሲሆን ከቤተሰቦቿ ጋር ሰበብሰብ ብለው ካሳለፉ በኋላ ነው ስድስት ልጆቿ ታመው ሆስፒታል እንዲገቡ የተደረገው።

    የዚህ ቤተሰብ አባል የሆኑ 20 ሰዎችም በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል።

    በአሜሪካ በኮሮኖቫይረስ ምከንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች ማህበራዊ መሰባሰቦች እንዲቀሩ እየመከሩ ይገኛሉ።

    ግሬስ ፋስኮን ጨምሮ ሶስት ልጆቿ የሞቱ ሲሆን "ይህ ለቤተሰቡ መቋቋም የማይችሉት ሐዘን ነው" ተብሏል።

    በአሜሪካ ከ200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሲሞቱ በ50 ግዛቶች ውስጥ 15ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተመዝግቧል።

    በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ሆስፒታሎች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ በማሰብ የእንቅስቃሴ ገደብ እየጣሉ ነው።

  13. ኮሮናቫይረስ ኑሮዎን ሥራዎን አስተጓጉሏል? ኢኮኖሚያዊ ጫናስ ፈጥሮብዎታል?

    በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ በሆነው ኮሮናቫይረስ ምክንያት በጥቂት ቀናት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ማጣታቸውን የአበባ አምራቾች ገለጹ።

    በየቀኑ እስከ 45ሺህ ዘንግ የሚጠጋ አበባ ለዓለም ገበያ ያቀርብ የነበረው አግሪ ሴፍት፤ ከማርች 15 በኋላ በመቋረጡ በየቀኑ 21200 የአሜሪካ ዶላር ወይም 678400 ብር እያጣ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።

    ድርጅቱ ሠራተኞቹን እረፍት እንዲወጡ እያደረገ ከመሆኑም በላይ በየቀኑ ወደ አንድ መቶ ሺህ የሚጠጋ የአበባ ዘንግ ወደ ኮምፖስተነት ለመቀየር ተገዷል።

    የዚህን ዘገባ ዝርዝር ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

  14. ስለ ኮሮናቫይረስ መረጃዎችን በዋትስአፕ አማካኝነት ያግኙ

    የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የሚመሩት ድርጅት ስለኮሮናቫይረስ ወቅታዊ መረጃዎችን በዋትስአፕ አማካኝነት ማድረስ መጀመሩን አስታወቁ።

    የዓለም የጤና ድርጅት በዋትስአፕ አማካኝነት በቀላሉ የቫይረሱን ስርጭት የሚያመላክቱ ወቅታዊ አሃዞችን፣ እንዴት ራስዎትን መጠበቅ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም የሚኖርዎት ጥያቄ ምላሽ ያገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች መረጃዎችንም ማግኘት ይችላል።

    አገልግሎቱን ለማግኘት የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።

    https://t.co/mUvOWlGfqC?amp=1

    ያስታውሱ በቅድሚያ ዋትስአፕ በስልክዎ ላይ መጫን ይኖርብዎታል።

  15. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መቼ ይቆማል?

    ክትባት፣ በቂ የሚባሉ ሰዎች ቫይረሱን መቋቋም የመቻል ተፈጥሯዊ መከላከያ ማዳበርና በዘላቂነት የግለሰቦችና የማህበረሰብ ባህሪ መቀየር ከኮሮናቫይረስ ቀውስ መውጫ ተብለው የተቀመጡ ነገሮች ናቸው።

    ዓለም የኮሮናቫይረስ ክትባት ላይ ለመድረስ ቢያንስ ከአመት እስከ ዓመት ተኩል የሚሆን ጊዜ ይወስድበታል።

    ከዚያም ክትባቱ ቢያንስ 60 በመቶ ለሚሆኑ ሰዎች ተሰጥቶ፣ እነዚህ ሰዎች ቫይረሱን የመከላከል አቅም አዳብረው ለቫይረሱ ተጋልጠው እንኳ የማይታመሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

    የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ በአሜሪካ ሰው ላይ ባለፈው ሳምንት ተሞክሯል።

    የዚህ ዓይነቱ ክትባት የሚፈለገውን ውጤት ብቻም ሳይሆን ያልተጠበቁ ሌሎች ኮሮናቫይረሶችን የማስከተል እድልም እንዳለው ሳይንቲስቶች እየገለፁ ነው። ለምሳሌ እንደ መደበኛ ጉንፋን ምልክት ያላቸውን ኮሮናቫይረሶች ሊያስከትል፣ በዚህም ሰዎች በተደጋጋሚ ሊያዙ ይችላሉ።

    ይህ ደግሞ በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ ለሆኑ ሰዎች አደጋ ይሆናል።

    የመጨረሻው አማራጭ የሰው ዘር በዘላቂነት ባህሪውን መቀየርና የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንደሆነ ሳይንቲስቶቹ ይናገራሉ። ይሀ እስካሁን እየተሰጡ ያሉ ምክር ሃሳቦችን በሙሉ መተግበርን እና በተደጋጋሚ የቫይረሱን ምርመራ ይጨምራል። ሰዎችን ዘወትር በለይቶ ማቆያ ማስቀመጥንም እንዲሁ።

    የዚህን ዘገባ ዝርዝር ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

  16. ኮሮናቫይረስና ወጣቶች

    በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 11ሺህ መድረሱን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት " ምንም እንኳ አዛውንቶች ለቫይረሱ ክፉኛ ተጋላጭ ቢሆኑም ወጣቶችም አያመልጡም" አለ።

    ዶ/ር ቴድሮስ፣ በበርካታ አገራት በእድሜ ከገፉ ሰዎች ተጋላጭ በመሆናቸው ብቻ በሚሰጡ የጤና ማሳሰቢያዎች ወጣቶች ቸል ማለት እንደታየባቸው ተናግረዋል።

    ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጄኔቫ ከሚገኘው ቢሯቸው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት " ምንም እንኳ አዛውንቶች ለቫይረሱ ክፉኛ ተጋላጭ ቢሆኑም ወጣቶችም አያመልጡም" ብለዋል።

    አክለውም ለወጣቶች መልዕክት አለኝ በማለት " ቫይረሱን ልትቋቋሙት አትችሉም። ቫይረሱ ለሳምንታት ሆስፒታል ሊያስተኛችሁ ከዚያም ሲያልፍ ልትሞቱ ትችላላችሁ። ባትታመሙ እንኳ ወዴት መንቀሳቀስ እንዳለባችሁ የምትወስኗቸው ውሳኔዎች ለሌሎች የሞትና የሕይወት ጉዳይ ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል።

    ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎች በቫይረሱ የሚያዙ መሆናቸውን ነው። ነገር ግን በእድሜ የገፉና ከዚህ ቀደም የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ይበለጥ ተጋላጭ ናቸው ተብሏል።