ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ኢራን
“ባህሪዋን እንድታስተካክል” ካስጠነቀቁ በኋላ፤ የአሜሪካ ጦር በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች አዲስ ጥቃት ከፈተ።
የአሜሪካ ጦር ባወጣው መግለጫ፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ
የሚያልፉ መርከቦች ጉዞን አደጋ ላይ ለመጣል ጥቅም ላይ የዋሉ "የኢራን
ወታደራዊ አቅሞች" ዒላማ መደረጋቸውን አስታውቋል።
ለ90 ደቂቃ በቆየው አዲስ ዙር ጥቃት በታላቁ
ቱንብ ደሴት የሚገኙ የኢራን የባሕር ዳርቻ መከላከያዎች እንዲሁም የክሩዝ ሚሳዔል ማከማቻ እና ማስወንጨፊያ ጣቢያዎች መመታታቸውን
ገልጿል።
የአራን “የዕዝ ማዕከላት፣ የፀረ-አውሮፕላን
መከላከያ ሥርዓቶች፣ የሚሳኤልና የድሮን አቅሞች እንዲሁም የባሕር ዳርቻ መከታተያ ተቋማት" ጥቃት ከደረሰባቸው የመከላከያ አቅም መካከል ተጠቅሰዋል። በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምትገኘው የባንደር አባስ ከተማም ዒላማ እንደሆነች ተነግሯል።
እነደ ጦሩ ገለጻ፤ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ
ጉዞ ላይ የጣለችውን እግድ በመጣስ ለማለፍ የሞከረ አንድ መርከብ ላይ ተተኩሷል።
ዋሽንግተን ይህንን ጥቃት ያደረሰችው ኢራን ባሕሬን
እና ኩዌት ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቷን ከገለፀች በኋላ ነው።
ለአምስተኛ ቀን የቀጠለው አዲስ ዙር የጥቃት ምልልስ
አገራቱ ጦርነቱን ለመቋጨት ገብተውት የነበረውን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት አደጋ ላይ ጥሎታል።
የኢራን ዋና ተደራዳሪ እና የፓርላማ አፈ ጉባኤ
መሀማድ ባገር ጋሊባፍ አገራቸው ከስምምነቱ የማትጠቀም ከሆነ ለውሉ የምትገዛበት “ምንም ምክንያት” እንደሌላት ለመንግሥት
መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን እስከሚቀጥለው
ሳምንት ድረስ ወደ ንግግር የማትመለስ ከሆነ ድልድዮችን እና የኃይል ማመንጫዎችን እንደሚመቱ ማክሰኞ ዕለት ዝተው ነበር።
ረቡዕ ዕለት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤
ይህንን ከማድረጋቸው በፊት ቀነ ገደብ ይሰጡ እንደሆነ ተጠይቀዋል። “ቀነ ገደብ ማስቀመጥ አልወድም፤ ነገር ግን እነሱ በደንብ ያውቃሉ፣
ታሪኩን ያውቁታል . . . ባህሪያቸውን ቢያስተካክሉ ይሻላቸዋል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በኋላ ላይ ደግሞ አሁን ኢራን "ደስተኛ
አይደለችም" ሲሉ በመከላከያ ጉባኤ ላይ ለተገኙት ልዑካን ተናግረዋል።
“ለመስማማት እጅጉን ይፈልጋሉ። እያደረግን ያለነውን
ነገር አልወደዱትም” ብለዋል። “የምንፈልገው ከእነርሱ ጋር መስማማት ነው ወይስ የጀመርነውን እናጠናቅቅ የሚለውን እንመለከታለን” ሲሉም
ተደምጠዋል።
የኢራኑ ዋና ተደራዳሪ ጋሊባፍ በበኩላቸው፤ የአገራቸው
ብሔራዊ ደኅንነት የተመሠረተው በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለውን “የኢራን አሰራር” በማስቀጠል ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከአሜሪካ ጋር “የኅልውና” ግጭት ውስጥ ያለችው
ኢራን ድርድርን የምትመለከተው ከጦርነት ጎን ለጎን እንዳለ የትግል ስትራቴጂ እንደሆነም አክለዋል።