የየመን ሁቲዎች የሳዑዲ አረቢያን የነዳጅ ማምረቻ ተቋማት እንደሚያጠቁ አስጠነቀቁ
ሁቲዎች ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የሚያካሂዱት ግጭት የሚባባስ ከሆነ የሳዑዲን የነዳጅ ተቋማት እና ሌሎች ወሳኝ ተቋማት ዒላማ እንደሚያደርጉ አስጠነቀቁ።
የሁቲ ታጣቂ ቡድን መሪ የሆነው አብዱል-ማሊክ ሁቲ እንደተናገረው "ሳዑዲ አረቢያ በአገራችን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት ግጭቱን የምታባብስ ከሆነ፣ ሁሉም የነዳጅ ማምረቻ ተቋማቷ እና ወሳኝ ማዕከላቷ የሚሳዔሎቻችን እና የድሮኖቻችን ዒላማ ይሆናሉ” በማለት አስጠንቅቋል።
ሰኞ ዕለት ሳዑዲ በሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ፈጽማለች በማለት ሁቲዎች የከሰሱ ሲሆን በምላሹም በሳዑዲ ውስጥ የሚገኝን ዒላማ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል አሁን እየተካሄደ ያለው የተኩስ ልውውጥ በአውሮፓውያኑ 2022 ከተደረሰው ተኩስ አቁም ወዲህ በመካከላቸው ያለው ውጥረት መባባሱን ያሳያል።
ሳዑዲ ተጨማሪ ጥቃት በሰነዓ ላይ የምትፈጽም ከሆነ ሪያድ የሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያዋ ዒላማ እንደሚሆን የሁቲ ታጣቂ ቡድን መሪ ማስጠንቀቁን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በሳዑዲ የሚደገፈው እና ኤደን ከተማ ውስጥ መቀመጫውን ያደረገው የየመን መንግሥት በሰነዓ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሁቲዎች አጋር የሆነችው የኢራን አውሮፕላን እንዳያርፍ ለማድረግ ነው ብሏል።
ወደ የመን የአየር ክልል የሚገቡ አውሮፕላኖች የቅድሚያ ፈቃድ በሳዑዲ ከሚመራው የአካባቢው አገራት ጥምረት ማግኘት እንዳለበት የሚያስገድደው አሠራር ከአስር ዓመታት በላይ በሥራ ላይ ቆይቷል።
የየመን መንግሥት እና ደጋፊዎቹ እንደሚሉት ይህንን የበረራ ፍቃድ ሁቲዎች እና ኢራን ከግዛቷ ቀጥታ በረራ በማድረግ ጥሰት እየፈጸሙ ናቸው ሲሉ ይከስሳሉ።
ማክሰኞ ዕለት ሁቲዎች በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት ያሰማራው የቅኝት ድሮንን መትተው መታላቸውን አሳውቀዋል።