ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስድስተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ 2013
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በትናንትናው ዕለት ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ተጀምሮ በአንዳንድ ቦታዎችም እስከ ሌሊት እንዲሁም በዛሬው ዕለትም እንዲሁ ድምፅ የሚሰጥባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በዚህ ምርጫ ለመሳተፍ ከትግራይ ክልል በስተቀር ከ37 ሚሊየን በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን የኢትጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል። 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ዕጩዎቻቸውን ለተወዳዳሪነት አቅርበዋል። በዚህ ምርጫ ዕጩዎች ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ይወዳደራሉ።
የቀጥታ ሽፋን
የምሥራቃዊ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል 'ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተካሂዷል' አለ
በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች በዛሬው ዕለት ድምጽ እየተሰጠ ነው
ምርጫ ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ሊካሄድባቸው ታስቦ በተለያዩ ምክንያቶች የድምጽ መስጠት ሂደቱ ሳይካሄድባቸው በቀሩት የምርጫ አካባቢዎች ዛሬ ማክሰኞ ድምጽ እየተሰጠባቸው መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
በትናንትናው ዕለት ባጋጠመ የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት ምክንያት ምርጫው ባልተካሄደበት የሲዳማ ክልል ውስጥ በሚገኙ በሁሉም ምርጫ ክልሎች ዛሬ ማክሰኞ ከጠዋቱ 5 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ እየተሰጠ ነው።
በጋምቤላ ክልልም ሰኞ ዕለት ይካሄዳል የተባለው ምርጫ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ተቋርጦ እንደነበር ያመለከተው ምርጫ ቦርድ፤ ዛሬ ማክሰኞ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ የመስጠት ሂደቱ ቀጥሏል ብሏል።
ከእነዚህ ባሻገር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሁለት ምርጫ ክልሎች ሲካሄድ የነበረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ለጊዜው የቆመ መሆኑን ቦርዱ አመልክቷል።
በዚህም ሳቢያ ለምርጫው የሚውሉ ቁሳቁሶች በሙሉ ታሽገው እንዲጠበቁ ቦርዱ ነወሰኑንና በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት ቦርዱ የሚደርስበትን ውሳኔ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
በዛሬው ዕለት መራጮች ድምጽ እየሰጡ ባሉባቸው የምርጫ ክልሎች ሂደቱ በዚሁ ዕለት እንደሚጠናቀቅ ነው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳወቀው።
ሰኞ ዕለት ያለምንም ችግር የድምጽ መስጠት ሂደት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተሰጡ ድምጾች ተቆጥረው ውጤት ይፋ እየተደረገ ይገኛል።
በሲዳማ ክልል ምርጫ እየተካሄደ ነው
ስድስተኛው ዙር ምርጫ ዛሬ እንዲካሄድ በተወሰነበት የሲዳማ ክልል ድምጽ የመስጠት ሥርዓት እየተከናወነ ነው።
በክልሉ ከ2 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎችም ክፍት እንደሆኑ የክልሉ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ፍሬው በቀለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ምርጫው በዛሬው ዕለት ረፋድ አምስት ሰዓት የተጀመረ ሲሆን እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ይቀጥላል ተብሏል።
ነገር ግን በክልሉ መዲና ሐዋሳ ምርጫ የተጠናቀቀ ሲሆን አንዳንድ ጣቢያዎችም የምርጫ ውጤቱን እየገለጹ ነው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት ከረፋድ አምስት ሰዓት ጀምሮ ድምጽ የሚሰጥባቸው ቦታዎች መኖራቸውን በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።
ቦርዱ ይህንን ያለው ትናንት ምሽት 5፡30 ላይ በሰጠው መግለጫ ነው።
በመግለጫውም ላይ የምርጫ ቦርድ አምስት አባላት መግለጫ ለመስጠት የተገኙ ሲሆን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫው "ከሞላ ጎደል እጅግ ጥሩ ነበር" ብለዋል።
የምርጫ ውጤት በአገሪቱ ባሉ ምርጫ ጣቢያዎች ደረጃ እየተገለጸ ነው
ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ድምጽ በተሰጠባቸውና ቆጠራ በተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ውጤት ለሕዝብ ይፋ እየተደረገ ነው።
የቢቢሲ ዘጋቢዎች ባሉባቸው በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በደሴ እና በባሕር ዳር ከተሞች ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ተካሄዶ በተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎች የተሰጠው ድምጽ ቆጠራ ትናንት ማታ መከናወኑ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት በተጠቀሱት ከተሞችና በሌሎችም አካባቢዎች በምርጫ ጣቢያዎች ደረጃ የድምጽ ቆጠራው ውጤት ለሕዝቡ ይፋ እየተደረገ ነው።
በምርጫ ጣቢያዎች ደረጃ የተገኘው ውጤት በአጠቃላይ የዕጩዎችን ውጤት ላያመላክት ስለሚችል በምርጫ ክልሉ ውስጥ ባሉ ጣቢያዎች ውስጥ የተገኙ ውጤቶች በቦርዱ አማካይነት ተሰባስበው ከተደመሩ በኋላ ነው ይፋዊው የድምጽ ቆጠራው ውጤት የሚታወቀው።
በምዕራብ ሸዋ ዞን በምርጫ ዕለት በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ሦስት ሰዎች ተገደሉ
ዛሬ ድምጽ የሚሰጥባቸው ቦታዎች መኖራቸው ተገለጸ
የስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ድምጽ መስጠት ሂደት ተጠናቀቀ
ሰላሳ ሰባት ሚሊዮን 408 ሺህ 600 ሕዝብ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገበበት በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲካሄድ ውሎ ድምጽ መስጠቱ ከምሽት ሦስት ሰዓት ላይ በይፋ ተጠናቋል።
በምርጫው 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 8ሺህ 209 ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤቶች ወንበሮች እንዲወዳደሩ ያቀረቡ ሲሆን በግል ደግሞ 125 ዕጩዎች ተፎካካሪ ሆነዋል።
በዕጩዎች ብዛት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተወዳዳሪዎችን በመላዋ አገሪቱ አቅርቧል። በተከታይነት በርካታ ዕጩዎችን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና እናት ፓርቲ ተፎካካሪዎችን አቅርበዋል።
ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ድምጽ የተሰጠው ለ445 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ሲሆን ጎን ለጎንም በየክልሎቹ ላሉት ምክር ቤቶች አባልነት ለሚወዳደሩ ዕጩዎች ድምጽ ተሰጥቷል።
ለቀሪዎቹ 64 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች ደግሞ ጳግሜን 01/2013 ዓ.ም ድምጽ ይሰጥባቸዋል። ቀሪው 38 መቀመጫ ደግሞ የትግራይ ክልል ወኪሎች ሲሆን ለጊዜው በክልሉ ውስጥ ባለው ችግር ምክንያት ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ አልታወቀም።
ዛሬ ሲካሄድ በዋለው የድምጽ መስጠት ሂደት በአንዳንድ ቦታዎች እክሎች እንደነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገለጹ ሲሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም አቤቱታዎች ቀርበውለት የማስተካከያ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደነበር የቦርዱ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ዛሬ ሲሰጥ የዋለው የመራጮች ድምጽ ምሽት ሦስት ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን የድምጽ ቆጠራው የድምጽ አሰጣጡ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚጀምር ሲሆን ነገ ማክሰኞ ጠዋትም ይቀጥላል።
ቢቢሲ አማርኛም የምርጫውን ሂደትና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙትን የቆጠራ ውጤቶች እየተከታተለ ማቅረቡን ይቀጥላል።
የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ውጤት መቼ ይታወቃል?
በደሴ እና በሐዋሳ የኢዜማ ተወካዮች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ 'ቅሬታቸውን' አሰሙ
የምርጫ ቦርድ አፈጻጸም ተስፋ ሰጪ ነው - ሽመልስ አብዲሳ
በምርጫው ሂደት ከጥቃቅን ችግሮች ውጭ የጸጥታ ችግር አለማጋጠሙን የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ አስታወቀ
በደቡብ ወሎ ዞን ምርጫው ያለምንም ችግር እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ለማ ከዞኑ ምርጫ ጽ/ቤት ኃላፊ ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት መግለጫ እስካሁን ሠላማዊ የሆነ ምርጫ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን ከፓርቲዎችና ከምርጫ አስፈጻሚዎች የቀረቡ አቤቱታዎች መኖራቸውን ኮማንደር ለማ ገልጸዋል።
በዞኑ በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች ላይም የተፈጠሩ ግለሰባዊ ግጭቶች፣ መራጮችን በገንዘብ የመደለል እና የመራጮችን በምስጢር ድምፅ የመስጠት ነጻነት የመንፈግ፣ የራሳቸውን የምርጫ ካርድ የመቅደድ ሁነቶች ነበሩ ብለዋል-ኮማንደሩ።
ዛሬ ምርጫ ያልተካሄደባቸው የተሁለደሬ ወረዳ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ምርጫ ጣቢያ የድምጽ መስጫ ወረቀት ሳጥን በመክፈት በተጠረጠሩ ሁለት ሴቶችና አራት ወንዶች ላይ ምርመራ መካሄዱንና ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስ መለቀቃቸውን ኮማንደር ለማ ገልጸዋል።
ምርጫ ቦርድ በእነዚህ ሁለት ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ወረቀት የያዘ ሳጥን በመከፈቱ ምርጫ እንደማይካሄድ ያስታወቀው ትናንት ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች የድምፅ መስጫ ወረቀት ሳጥን ተሰንጥቋል በሚል የቀረቡ ቅሬታዎች ተጣርተው ‘ለአደጋ የተጋለጡ ባለመሆናቸው’ ወደ ምርጫ መገባቱን ገልጸዋል።
በደላንታ ወረዳ 031 ቀበሌ አንድ ግለሰብ ለሁለት ሰዎች 600 ብር መደለያ ሲሰጥ በመገኘቱ ከተቀባዩ አንዱ ሰው እና ሰጭው ሲያዙ አንደኛው ማምለጡን ኮማንደሩ አክለዋል።
በጃማ ወረዳ ሁለት የመንግሥት ሠራተኞች ምርጫ የሚሰጥበትን ክፍል ድንጋይ በመቀጠል በምስጢር ድምፅ የሚሰጡ መራጮችን ነጻነት በመንፈጋቸው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ብለዋል ኮማንደር ለማ።
ኮማንደር ለማ እንደገለፁት በከላላ እና መካነሰላም ሁለት ሴቶች የምርጫ ካርዳቸውን በመቅደዳቸው ምርመራ ተካሂዶ በዋስ ተለቀዋል።
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅም የጸጥታ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮማንደር ለማ ተናግረዋል።
በምርጫው ሂደት ከጥቃቅን ችግሮች ውጭ የጸጥታ ችግር አለማጋጠሙን የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ አስታወቀ
የዞኑ የምርጫ ቦርድ ዋና አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ መኮንን በበኩላቸው በዞኑ በሚገኙ ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች እምብዛም ያጋጠመ ችግርእንደሌለ ተናግረዋል።
በአብዛኛው የዞኑ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ የመስጠት ሂደቱ ቀጥሏል ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን 22 የምርጫ ክልሎች የነበሩ ሲሆን በሦስቱ [አምባሰል፣ ተሁለደሬ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት] ባጋጠመ ችግር ምርጫ እንዳይካሄድ በምርጫ ቦርድ መወሰኑን አቶ ብርሃኑ አስታውሰዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን 1515 ምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙም አስተባባሪው ገልጸዋል።
የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እስከ ምሽቱ 3፡00 ድረስ ተራዘመ
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓትድምጽ መስጠት ሂደቱ መራዘሙን ተናገሩ።
አመሻሽ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የኮምዩኒኬሽን አማካሪዋ እንዳሉት በመላው አገሪቱ ውስጥ ምርጫ እየተካሄደ ባለባቸው ጣቢያዎች ሁሉ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እስከ ምሽቱ 3:00 ሰዓት ድረስ ይቀጥላል።
በአዲስ አበባ፣ አዳማ እና በሐዋሳ ቢቢሲ ተዘዋውሮ የተመለከታቸው አካባቢዎች ላይ መመልከት እንደተቻለው አሁንም ለመምረጥ የሚጠባበቁ ሰዎች ረዣዥም ይዘው የሚገኙባቸው እንዲሁም የምርጫ ወረቀት እጥረት በማጋጠሙ መራጮች ለረዥም ሰዓት እንዲጠብቁ የተገደዱባቸው ጣቢያዎች ነበሩ።
ሶሊያና እንዳሉት በተለያየ ምክንያት በድምጽ አሰጣጥ ሂደት ላይ የተፈጠሩ መዘግየቶችን ተከትሎ ድምጽ አሰጣጡ ተራዝሟል።
መራጮችም ሂደቱ መራዘሙን ተገንዝበው በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምጽ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢዜማ ምርጫው ከመጠቃለሉ በፊት መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ጉዳይ አመለከተ
የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ውጤት መቼ ይታወቃል?
በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው። በዚህ ምርጫ ላይ በክልሎችና በፌደራል ምክር ቤቶች ውስጥ ላሉ መቀመጫዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች ይፎካከራሉ።
ዛሬ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ማለዳ ላይ የጀመረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ቀን ሙሉ ሲካሄድ ውሎ፤ ሌላ ተጨማሪ መመሪያ ከምርጫ ቦርድ አስካልተሰጠ ድረስ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል።
የድምጽ መስጠት ሂደቱ እንዳበቃ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የሕዝብ ታዛቢዎች የዕጩ ታዛቢዎች በሚገኙበት የድምጽ ቆጠራው ይጀመራል።
በቅድሚያ ደምጽ በየምርጫ ጣቢያው ይቆጠራል። ነገር ግን በጸጥታ መደፍረስ ወይም ተመሳሳይ አስገዳጅ ምክንያት ሲከሰት የምርጫ ጣቢያው የምርጫ አስፈፃሚ ለምርጫ ክልሉ ጥያቄ አቅርቦ ሲፈቀድ ወይም የምርጫ ክልሉ የምርጫ አስፈፃሚ ሲወስን የድምጽ ቆጠራው በምርጫ ክልሉ ጽህፈት ቤት ይካሄዳል። ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ https://bbc.com.im/amharic/news-57554215%3C/p%3E%3C/div%3E%3C/div%3E%3C/article%3E%3C/li%3E%3Cli class="css-xxlek1">
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኤርትራና ሱዳን ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጡ እየሰሩ መሆኑን ገለጹ
ኦባሳንጆ የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን በመያዝ የምርጫ ጣቢያዎችን ጎበኙ
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ የሚታዘበውን የአፍሪካ ሕብረት ቡድን እየመሩ ነው።
ኦባሳንጆ በአዲስ አበባ ምርጫ የሚደረግባቸውን ጣቢያዎች፣ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ደምጽ የሰጡበትን ጣቢያን ጨምሮ እየተዘዋወሩ መጎብኘታቸው ተዘግቧል።
ምርጫ 2013 ለኢትዮጵያና ለአካባቢው አገራት ምን ይዞ ይመጣል?
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ምርጫው ሠላማዊና ነጻ እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሁሉም መራጮች “በነጻነትና በሠላማዊ ሁኔታ” ድምጻቸውን መስጠት እንዲችሉ እንዲያደርጉ ጠየቁ።
ዋና ጸሐፊው ጨምረውም በምርጫው የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ከግጭትና ግጭትን ከሚያነሳሱ ተግባራት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።
አንቶኒዮ ጉቴሬስ መልዕክታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ ነው ያሰፈሩት።
ዛሬ ማለዳ መካሄድ የጀመረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ምርጫው በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እየተካሄደ ነው።
አስካሁን ባለው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የጎላ ችግር እንዳላጋጠመ ምርጫውን የሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ አስታውቀዋል።
የምርጫ ታዛቢዎች ምን ይላሉ?
በደሴ ከተማ ባሉ 104 የምርጫ ጣቢያዎች የሚወዳደሩ ፓርቲዎች አንድ ወይም ሁለት ታዛቢዎችን አስቀምጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከሲቪል ሶሳይቲ የመጡ ነዋሪዎች ምርጫውን እየታዘቡ ነው።
በፒያሳ ክፍለ ከተማ ለ2 ምርጫ ጣቢያ ኢዜማ ፓርቲን ወክለው ምርጫውን እየታዘቡ የሚገኙት አቶ ተሾመ መሐመድ፤ እየታዘቡ ባሉበት ጣቢያ እስካሁን ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ አረጋውያን መራጮችን ማስረዳትና ማመላከት አስቸጋሪ ነበር ብለዋል።
ሌላኛው የእናት ፓርቲ ታዛቢ ሻምበል ወንድሙ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ጥሩ ቢሆንም በጣቢያው ቅሬታ ሰሚ አለመመደቡን ገልጸዋል። “ቅሬታ ሰሚዎች አለመመደባቸውም ጥያቄ ፈጥሮብኛል” ብለዋል።
እታገኝ ማሞ ደግሞ በባንቧ ውሃ ክፍለ ከተማ ቀጠና 7 ምርጫ ጣቢያ የአብን ታዛቢ ናቸው። በጣቢያቸው ከማለዳ ጀምሮ የምርጫ ሂደቱን እየታዘቡ ይገኛሉ።
“እስካሁን ያለው ነገር ጥሩ ነው፤ ምንም ያጋጠመ ችግር የለም” ብለዋል።
ቢኒያም በፒያሳ ክፍለ ከተማ ለ14 ምርጫ ጣቢያ የእናትፓርቲ ታዛቢ ነው። “እስካሁን ድረስ ያጋጠመ ችግር የለም። ያው የምርጫ ወረቀት ተሳስቶ መጥቶ ነበር። ለሚመለከተው አሳውቀን ችግሩ ቶሎ ተፈቷል” ብሏል።
ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር በመነጋገር ችግሮችን እየፈታን ነው የሚለው ቢኒያም፤ የድምጽ አሰጣጥ ሒደቱ ሠላማዊ እንደሆነ ተናግሯል።