አውስትራሊያ የክትባት ሙከራው ከተሳካ ለዜጎቿ በነፃ ለመስጠት ቃል ገባች
አውስትራሊያ ተስፋ የጣለችበት የኮሮናቫይረስ ክትባት ከተሳካ ለ25 ሚሊየን ሕዝቦቿ ክትባቱን በነፃ ለመስጠት ቃል ገባች።
ክትባቱ እየተሰራ ያለው በመድሃኒት አምራቹ ኩባንያው አስትራዜኔካ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ነው። የክትባቱ ሙከራ ከተሳካና ከኩባንያው ጋር ስምምነት ላይ ከተደረሰ በቅድሚያ ለአውስትራሊያዊያን በነፃ እንደሚሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሶን ተናግረዋል።
ኦክስፎርድና አስትራዜኔካ እየሰሩ ያሉት ይህ ክትባት ወደ መጨረሻው ደረጃ ለመድረስ ተስፋ ከተጣለባቸው አምስት ክትባቶች መካከል አንዱ ነው።
በመሆኑም “ክትባቱ ስኬታማ ከሆነ በቀጥታ በራሳችን ማምረትና ማቅረብ እንጀምራለን፤ ከዚያም ለ25 ሚሊየን አውስትራሊያ ሕዝቦች በነፃ እንሰጣለን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ለሁሉም ሕዝብ ክትባቱ ለማቅረብ ምን ያህል ሊያስወጣ እንደሚችል ያልተወሰነ ቢሆንም አውስትራሊያ ከአሜሪካው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ከቤክቶን ዲኪንሰን ጋር 100 ሚሊየን መርፌዎች አቅርቦት የ25 ሚሊየን ዶላር ስምምነት ተፈራርማለች።
አውስትራሊያ የክትባት ስምምነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈራረመችውም ከአስትራዝኔካ ጋር ነው ተብሏል።
በአውስትራሊያ እስካሁን ከ400 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። በዚህ ወር መጀመሪያ ቪክቶሪያ ግዛት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች ሲሆን ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብም ጥላለች።
በግዛቷ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ይህም በግዛቷ ስጋትን ፈጥሯል።