በጀርመን የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ ሠራተኛ ለሩሲያ ሲሰልል እንደነበር አመነ

ዴቪድ ስሚዝ

የፎቶው ባለመብት, JULIA QUENZLER

የምስሉ መግለጫ, ዴቪድ ስሚዝ
ታትሟል

ዴቪድ ስሚዝ የተባለ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጋ የኤምባሲ ጥበቃ ለሩሲያ ሲሰልል እንደነበረ አመነ። 

የ58 ዓመቱ ስሚዝ በበርሊን የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ኤምባሲ ውስጥ በጥበቃ አባልነት ይሠራ በነበረበት ዘመን ነው ለሩሲያ ሲሰልል የነበረው።

ስሚዝ ጀርመን በርሊን ውስጥ በሚገኘው የአገሩ ኤምባሲ ለስምንት ዓመታት በጥበቃ አባልነት አገልግሏል።

ለሩሲያ ሲሰልል የነበረውም ሆን ብሎ፣ አቅዶ እና አልሞ አገሩን እና ኤምባሲውን ለመጉዳት እንደነበረ ተናግሯል ይላል ዐቃቤ ሕግ። 

በእነዚህ ዘመናት ቁልፍ መረጃዎችን እና የኤምባሲውን ምሥጢሮችን ለሩሲያ አሳልፎ ሲሰጥ ነበር ተብሏል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ ድርጊቱን ለመፈጸም ያነሳሳው ምክንያት ለተመሳሳይ ጾታ ባለው ሥር የሰደደ ጥላቻና አገሩ ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ በተቃራኒው  የተመሳሳይ ጾታ ባንዲራን ከፍ አድርጋ በማውለብለቧ እንደሆነም ተናግሯል። 

ግለሰቡ እነዚህን መረጃዎች ለሩሲያ በማሾለክ ዩክሬን አልያም ሩሲያ ሄዶ ቀሪ ዘመኑን ለመኖር ይመኝ እንደነበርም ተነግሯል። 

ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ሲውል ፖስትዳም፣ ጀርመን በሚገኘው መኖርያ ቤቱ 800 ዩሮ ተገኝቷል ብሏል ዐቃቤ ሕግ።

በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው ፍርድ ቤት ስሚዝ ላይ ገና ብይን ያላስተላለፈበት ቢሆንም፣ ጥፋተኛ ሆኖ ካገኘው እስከ 14 ዓመት ሊፈረድበት እንደሚችል ተገምቷል። 

በስሚዝ ላይ የተመሠረተው የክስ ዶሴ እንደሚያሳየው ከሆነ በፈረንጆቹ 2020 በበርሊን ከሩሲያው የጦር መኮንን ሜጀር ጄኔራል ሰርጌይ ቹኩሮቭ ጋር ተገናኝቶ መረጃን ተለዋውጧል።  

ተጠርጣሪው ስሚዝ ያቀበለው መረጃ በዩኬ የሚገኙ ሠራተኞችን ስም ዝርዝር እና ሙሉ አድራሻን የያዘ ሰነድ ነው።

ከዚህ ሌላ በበርሊን የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲን አሠራር፣ የመረጃ አያያዝና የኤምባሲውን የውስጥ ይዘትን የተመለከተ ዝርዝር መረጃን አቀብሏል።

ይሁንና ስሚዝ የጥበቃ ሠራተኛ ስለነበረ ሁነኛ የሚባሉ ቁልፍ መረጃዎችን ሊያገኝ አልቻለም።

ስሚዝ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ዕለት ከሥራ ቦታ የቀረው አሞኛል በሚል ሰበብ ነበር።

ዩኬ ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጣት በጠየቀችው መሠረት ጀርመን ለዩኬ ግለሰቡን ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ አሳልፋ መስጠቷ ይታወሳል።