"እህቴ ማሕጸኗን ሰጥታኝ 'ተዓምረኛ' ልጅ ወለድኩ"

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በዩናይትድ ኪንግደም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሌላ ሴት በተለገሰ ማሕጸን ልጅ ተወልዳለች።

'ተዓምረኛ' የተባለችው ልጅ የተወለደችው ግሬስ ዴቪድሰን የተባለችው የ36 ዓመት እናት ከእህቷ በተሰጣት ማሕጸን አማካይነት ነው።

ግሬስ ማሕጸኗ ጽንስ መሸከም ስለማይችል ከእህቷ በ2023 ማሕጸን ተለግሷታል።

ግሬስና ባለቤቷ አንገስ 'ተዓምረኛዋን' ጨቅላ ኤሚ ብለው ሰይመዋታል። ለግሬስ ማሕጸኑን የለገሰቻት እህቷ ስሟ ኤሚ ስለሆነ ነው ለልጅቷም ተመሳሳይ ስም የተሰጣት።

ሕጻኗ ኤሚ ሁለት ኪሎግራም ትመዝናለች።

ኤሚ በተለገሰ ማሕጸን የተወለደች የመጀመሪያዋ ልጅ ሆና በዩኬ ተመዝግባለች።

እናቷ ግሬስ እንደምትለው፣ በዩኬ በልገሳ ማሕጸን የተወለደች የመጀመሪያዋ ልጅ እናት መሆን "አስደናቂና ለማመን የሚከብድ" ነው።

"ስትወለድ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚኖረን ለመገመት ከባድ ነበር። በጣም አስደናቂ ነገር ነው" ስትል ግሬስ ስሜቷን ገልጻለች።

ግሬስ እና አንገስ በሰሜን ለንደን ነው የሚኖሩት። ግሬስ ከእህቷ በተለገሳት ማሕጸን ሁለተኛ ልጅ ለመውለድ ታስባለች።

ቀዶ ሕክምናውን ያደረገው የሐኪሞች ቡድን ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ ግሬስ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ሦስት ተመሳሳይ ቀዶ ሕክምናዎች ለእናቶች ተደርገዋል። እነዚህ ቀዶ ሕክምናዎች የተከናወኑት ሕይወታቸው ካለፈ ማሕጸን ለጋሾች በተወሰዱ ማሕጸኖች ነው።

ተጨማሪ 15 ቀዶ ሕክምናዎች ለማድረግ የሐኪሞች ቡድኑ አቅዷል።

ግሬስ፣ ማይር-ሮኪታንስኪ-ኩስተር-ሀውሰር የተባለ ሕመም ስላለባት ማሕጸኗ ጽንስ ለመሸከም አይችልም።

ከእናቷ ማሕጸን ለመውሰድ አቅዳ የነበረ ቢሆንም ተመጣጣኝ ሆኖ ስላልተገኘ ከእህቷ ወስዳለች።

እህቷ ኤሚ ሁለት ልጆች ስለወለደችና ተጨማሪ ልጆች ስለማትፈልግ ማሕጸኗን ለመለገስ ፈቅዳለች።

እህትማማቾቹ ከቀዶ ሕክምናው በፊት የሥነ ልቦና ምክር አግኝተዋል።

ግሬስ በማደጎ ልጅ የማሳደግ ወይም ጽንሱን በሌላ ሴት ማሕጸን ውስጥ አሳድጎ ልጅ የማግኘት አማራጭ ተሰጥቷት ነበር።

"እናት መሆን የሁሌም ምኞቴ ነበር። ግን እናት መሆን እንደማልችል ስለማውቅ ለዓመታት ፍላጎቴን ደብቄ ኖርኩ" ትላለች ግሬስ።

በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በልገሳ ማሕጸን ልጅ የተወለደው በ2014 በስዊድን ነበር።

ከዚያ ወዲህ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሕንድና ቱርክን ጨምሮ በተለያዩ አገራት 135 የማሕጸን ቀዶ ሕክምናዎች ተደርገዋል።

65 የሚደርሱ ልጆችም ተወልደዋል።

የኤሚን ማሕጸን ለግሬስ በቀዶ ሕክምና ለማስተላለፍ ከ30 በላይ የሕክምና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። 17 ሰዓት የወሰደ ቀዶ ሕክምናም ተከናውኗል።

በኦክስፎርድ፣ በቸርችል ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ቡድኑን የመራችው ኢዛቤል ኩዊሮጋ እንዳለችው ቀዶ ሕክምናው በሁለቱም እህትማማቾች ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም "ሕይወትን የፈጠረ ሆኗል" ስትል ገልጻዋለች።

"ሕይወትን ከመስጠት የበለጠ ነገር የለም" ብላለች ኢዛቤል።

ኤሚ ማሕጸኗን ከለገሰች በኋላ እህቷ ግሬስ ወልዳ ስላየች ማሕጸኗን የማጣት ስሜት እንዳልተሰማት ትናገራለች።

ግሬስ ማሕጸኑ በተለገሳት በሁለት ሳምንት ውስጥ የወር አበባ አይታለች። በአይቪኤፍ የመጀመሪያ ዙር ሙከራም ጸንሳለች።

"ልጄ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሕጸኔ ውስጥ ስትንቀሳቀስ ልዩ ስሜት ነበር የተሰማኝ። አጠቃላይ እርግዝናው ልዩ ነበር" ብላለች ግሬስ።

'ተዓምረኛዋ' ሕጻን ኤሚ የተወለደቸው በቀዶ ሕክምና ነው።

ግሬስ እና አግነስ ሁለተኛ ልጅ ከወለዱ በኋላ ግሬስ የተለገሳት ማሕጸን ከሰውነቷ በቀዶ ሕክምና እንዲወጣ ይደረጋል።

አሁን ላይ ሰውነቷ የእህቷን ማሕጸን አልቀበልም እንዳይል የሕክምና ክትትል እተደረገላት ነው።

ለዚህ የምትወስደው መድኃኒት ዘለግ ላለ ጊዜ ከተዋጠ ለካንሰር ሊያጋልጥ ስለሚችል የተለገሳት ማሕጸን መውጣት ይኖርበታል።

በኢሜፔሪያል ኮሌጅ ለንደን የሥነ ተዋልዶ ሐኪም ፕ/ር ሪቻርድ ስሚዝ የማሕጸን ቀዶ ሕክምና ላይ ጥናት ሠርተዋል።

የኤሚን ማሕጸን ለግሬስ በመስጠት ሒደት ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወቱት ፕሮፌሰሩ በስኬታቸው ደስተኛ ናቸው።

በዩኬ ከ15,000 በላይ ማሕጸናቸው ጽንስ መሸከም የማይችል ሴቶች ተስፋ አግኝተዋል ብለው ያምናሉ። ከእነዚህ መካከል 5,000 ያህሉ ያለ ማሕጸን ነው የተወለዱት።

ባለሙያው የማሕጸን ልገሳ ላይ የሚሠራ የተራድኦ ድርጅትም አላቸው። የግሬስን የሕክምና ወጪ የሸፈነው ይህ ድርጅት ሲሆን ሐኪሞቹም በነጻ ነው አገልግሎቱን የሰጡት።

10 ሴቶች እንቁላል አስቀምጠው የጽንስ ሕክምና እስከሚደረግላቸው እየጠበቁ ሲሆን እያንዳንዱ ሕክምና 30,000 ፓውንድ ያስወጣል።

የቀዶ ሕክምና ቡድኑ 15 የተለገሰ ማሕጸን ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይችላል። ከእነዚህ አምስቱ በሕይወት ካሉ ሴቶች የሚወሰዱ ሲሆን አሥሩ ደግሞ ከሞቱ ሴቶች የሚወሰዱ ናቸው።

ሕይወታቸው ካለፈ ሴቶች የሚወሰድ ማሕጸን የቤተሰብ ፈቃድ ይጠይቃል።

ግሬስ እና አግነስ ልጅ እንዲያገኙ ማሕጸን የለገሰችውን ኤሚ "ለማመስገን በቂ ቃላት የሉንም" ይላሉ።

ሕጻኗን በኤሚ ስም የሰየሙት ደስታቸውን ለመግለጽ ነው።

ሕጻን ኤሚ፣ ሌላው ስሟ መሪ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዋን ለመዘከር ኢዛቤል ሆኗል።

ግሬስ በእህቷ ማሕጸን ልጅ መውለዷ ከእህቷ ጋር የበለጠ እንድትቀራረብ አድርጓታል።

"ማሕጸኗን እንድትለግሰኝ መጠየቅ ቀላል ነገር አልነበረም። ትልቅ የእህትነት ፍቅር አሳይታኛለች" ትላለች ግሬስ።