የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከመንግሥት የሰላም ንግግር ጥያቄ አልቀረበልኝም አለ

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የትጥቅ ግጭት ውስጥ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሰላም ንግግር ጥያቄ ከመንግሥት አልቀረበልኝም አለ።
አማጺው ቡድን ይህን ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ ማክሰኞ መጋቢት 19/2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከታጣቂው ጋር ንግግር ለማድረግ መንግሥታቸው ያደረገው በርካታ ጥረት አለመሳካቱን ከተናገሩ በኋላ ባወጣው መግለጫ ነው።
መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ያሰሙት ንግግር የሰላም ጥረቱን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ አይደለም ብሏል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮችን ለማግኘት ተደርጓል የተባለው ጥረት ከልብ የመነጨ ጥረት አይደለም ያለው ታጣቂ ቡድኑ፤ “ይልቁንም መንግሥት የአካባቢ ሰዎችን በኮሚቴ በማዋቀር የቡድኑ አባላት ትግል ጥለው እንዲገቡ ለማግባባት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል” ብሏል።
መሰል ጥረቶች ወደፊት ሊኖሩ የሚችሉ የሰላም ንግግር ዕድሎችን ሊያጨናግፋ ይችላሉ ያለው አማጺ ቡድኑ፤ አሁንም በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ለሰላም ንግግር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ውሏቸው መንግሥታቸው ለሰላም ንግግር ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ለመነጋገር በሚያደርገው ጥረት ቡድኑ ማዕከላዊ የሆነው ዕዝ ስለሌለው ሂደቱ አዝጋሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ የተዋቀረ ኃይል ባለመኖሩ ከተለያዩ ኃይሎች ሃሳቦች በመቅረባቸው ሂደቱ ተጓትቷል ብለዋል።
ታጣቂ ቡድኑ ግን መንግሥት ቡድኑ ማዕከላዊ ዕዝ የለውም የሚል “አዲስ ፕሮፖጋንዳ ከማሰማት ይቆጠብ ብሎ የቡድኑ አመራር ማን እንደሆነ በአግባቡ ይረዳል” ብሏል።
የሰላም ንግግር ጥረት
የፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር ሰላም ለማውረድ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወደ ሰላም የሚመጣ ከሆነ ለሰላም ንግግር በራቸው ክፍት መሆኑን ገልጸው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥሪውን በአውንታዊነት እንደሚመለከተው በመግለጽ፣ ለድርድሩ ስኬታማነት ያስፈልጋሉ ያላቸውን ጉዳዮች፣ ፍላጎቱን እና የንግግር ቅድመ ሁኔታዎችን አሳውቆ ነበር።
ገለልተኛ የሆኑ ሦስተኛ ወገን የውጭ አሸማጋዮች እንዲኖሩ፣ ከኦሮሚያ ክልል አስተዳደር በተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱ ተሳታፊ እንዲሁን፣ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ካቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት
ምንም እንኳ በሁለቱም ወገኖች መካከል የሰላም ንግግር ፍላጎት እንዳለ ቢገለጽም አስካሁን በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሉ መካከል ግጭት በማስቆም ሰላም የሚያመጣ ተጨባጭ እርምጃ ሳይወሰድ ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት ጉዳዮች ያሳስበናል ያሉ ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁለቱን አካላት የአፍሪካ ኅብረት እንዲያሸማግል ባለፈው ሳምንት ጥያቄ አቅርበዋል።
አስራ ሁለት ገዢውን የብልጽግና ፓርቲን ወክለው ከኦሮሚያ ክልል ተመርጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑት እንደራሴዎች፤ በክልሉ እየተካሄደ ያለው ግጭት ሕይወት እየቀጠፈ እና ንብረት እያወደመ በመሆኑ፣ የአፍሪካ ኅብረት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለማስቆም እንዳረገው ሁሉ፣ በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ችግር በማሸማገል እንዲረዳ ጥያቄ አቅርበዋል።
ጥያቄውን ያቀረቡት የምክር ቤት አባላት አስተባባሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ደገፋ ከዚህ ቀደም ችግሩን በንግግር ለመፍታት ፍላጎት እንዳለ በሁለቱም ወገኖች የተገለጸ ቢሆንም ተጨማባጭ እርምጃ ባለመወሰዱ የአፍሪካ ኅብረት በአሸማጋይነት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቄ መቅረቡን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በውጭ አገራት ያሉ እና የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ እንዲገቡ በቀረበው ጥሪ መሠረት በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገር ቤት መግባታቸው ይታወሳል።
ከእነዚህም መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንዱ ሲሆን፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከዚሁ ቡድን በመለየት በትጥቅ እንቅስቃሴው ቀጥሏል። ባለፉት አራት ዓመታትም ቡድኑ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በስፋት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ታጣቂ ቡድኑ በርካታ ንሑሃንን፣ የመንግሥት ባለስልጣናትን በመግደል እና በማፈናቀል እንዲሁም በዘረፋ ይከሰሳል።
መንግሥት ‘ሸኔ’ ሲል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከሁለት ዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሽባሪ ቡድን” ተብሎ መፈረጁ ይታወሳል።












