በሩሲያ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ወታደራዊ መጓጓዥ አውሮፕላኖች ተመቱ

ኢል-76 ወታደራዊ መጓጓዣ አውሮፕላኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በሰሜን ምዕራብ ሩሲያ በፕስኮቭ ከተማ የደረሰ የድሮን ጥቃት ሁለት ወታደራዊ መጓጓዣ አውሮፕላኖችን መምታቱን የሩሲያ የዜና ወኪሎች ዘገቡ።

ኢልዩሺን 76 የተባሉት መጓጓዣ አውሮፕላኖች በጥቃቱ ምክንያት እሣት እንደያዙ ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ግዙፍ የእሣት ነደድ ያለበት እና የፍንዳታ ድምፅ የሚሰማበት ቪድዮ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የለጠፉት የግዛቱ አስተዳደር እንደገለጡት ጦር ሠራዊቱ ጥቃቱን መክቷል።

ከተማዋ ከዩክሬን 600 ኪሎ ሜትር ርቃ ለኢስቶኒያ ድንበር ቀረብ ብላ የምትገኝ ናት።

ብዙዉን ጊዜ ሩሲያ ውስጥ ጥቃት ሲፈፀም ድምፅ የማታሰማው ዩክሬን እንደተለመደው ስለዚህኛው ጥቃት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

ነገር ግን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሩሲያ ግዛት የተለያዩ የድሮን ጥቃቶች እያደረሰች እንዳለ ይታመናል።

የፕስኮቭ አስተዳዳሪ ሚካሄይል ቬዴሪንኮቭ በቴሌግራም በለጠፉት ፅሑፍ “ጦር ሠራዊቱ በፕስኮቭ አየር ማረፊያ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እየመከተ ነው” ብለዋል።

ጥቃቱ በደረሰበት ስፍራ እንደነበሩ የሚናገሩት አስተዳዳሪው “የመጀመሪያ ዙር ምርመራዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” ሲሉ ጠቁመዋል።

የሩሲያው ዜና ወኪል ታስ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ዋቢ አድርጎ ባወጣው ዘገባ አራት ኢል-76 የተባሉ አውሮፕላኖች ጉዳት ሲደርስባቸው ሁለቱ “በእሣት ጋይተዋል” ብሏል።

ሪያ የተሰኘው የዜና ወኪል ደግሞ ሁለት አውሮፕላኖች እሣት መያዛቸውን አስነብቧል።

ባለፈው ግንቦት በተመሳሳይ የፕስኮቭ ከተማ የድሮን ጥቃት ዒላማ ሆና ነበር።

ባለፈው ሳምንት በሩሲያዋ ቤልጎሮድ ክልል በደረሰ የድሮን ጥቃት ሶስት ሰዎች መገደላቸው ሲዘገብ ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎ በሩሲያዋ መዲና የድሮን ጥቃት እንደተቃጣ ተሰምቷል።

ከቀናት በፊት የሩሲያ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በሴንይት ፒተርስበርግ ከተማ በዩክሬን ድሮን ጥቃት ከጥቅም ውጭ መሆኑ ተገልጧል።

ምንም እንኳ ዩክሬን እኒህን የድሮን ጥቃቶች እያደረሰች እንደሆነ ባትናገርም ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በሩሲያ ግዛት ጥቃት መድረሱ “የማይቀር ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

በሌሎች የዩክሬን ጦርነት ዜናዎች የሩሲያ ጦር 50 ያክል የዩክሬን ወታደሮች የጫኑ መርከቦችን ጥቁር ባሕር ላይ መደምሰሱን ገልጧል።

ዩክሬን ስለጥቃቱ አስተያየት ባትሰጥም በሞስኮው ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ለሊት አካባቢ ሞስኮው መርከቦቹን እንደመታች ተገልጧል።

የሩሲያ ጦር ሠራዊት አክሎ በደቡባዊቷ ብራያንስክ ግዛት እና በማዕከላዊ ኦርዮል ዩክሬን ልታደርስ የነበረውን የድሮን ጥቃት አምክኛለሁ ብሏል።

የሩሲያው ታስ የዜና ወኪል ሞስኮው የሚገኘው የቭኑኮቮ አየር ማረፊያ ለጊዜው መዘጋቱን አስነብቧል።