በጣሊያን ባሕር ዳርቻ በሰጠመችው ጀልባ የሞቱት ስደተኞች ቁጥር ከ100 በላይ ሊሆን ይችላል ተባለ

ስደኞችን ያሳፈረች ጀልባ በጣሊያን ባሕር ዳርቻ ሰጥማ ቢያንስ 59 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በደቡባዊ ጣሊያን ባሕር ዳርቻ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ በሰጠመችው ጀልባ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።

በደቡባዊ ጣሊያን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ እሁድ ዕለት በደረሰው በዚህ አደጋ በርካታ ሕጻናትን ጨምሮ አስካሁን 62 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።

ካላብሪያ ከተባለችው የባሕር ዳርቻ የመዝናኛ ክልል አቅራቢያ በአደጋው የሞቱ ሰዎች አስከሬን የተገኘ ሲሆን፣ ከሟቾቹ መካከልም አንድ ጨቅላን ጨምሮ 12ቱ ልጆች መሆናቸው ተዘግቧል።

የጣሊያን ባለሥልጣናት በጀልባዋ ተሳፍረው ከነበሩት መካከል የደረሱበት ያልታወቀ በመኖራቸው የሟቾች ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በጀልባ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎች ቁጥር እስካሁን በትክክል አልታወቀም። በጀልባዋ ተሳፍረው የነበሩ እና በሕይወት የተረፉ ስደተኞች ግን ጀልባዋ ላይ 150 ሰዎች ተሳፍረው ነበር ብለዋል።

ሕይወት አድን ሠራተኞች ደግሞ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል “ከ200 በላይ ሰዎች” ጀልባዋ ላይ ነበሩ ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ማለት የጠፉ ሰዎች ቁጥርን ከ60 በላይ ያደርገዋል።

አደጋው ወዳጋጠመበት ካላባሪያ ግዛት የተጓዙት የጣሊያን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ማቴዎ ፒአንቴዶሲ ቢያንስ እስከ 30 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም ብለዋል።

የጣሊያኑ አንሳ የዜና ወኪል ከሟቾች መካከል የጥቂት ወራት ዕድሜ ያላት ጨቅላ ትገኝበታለች ብሏል።

የጣሊያን የባሕር ዳርቻ ጠባቂዎች 80 ሰዎች በሕይወት መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ጀልባዋ ከበርካታ ቀናት በፊት የአፍጋኒስታን፣ የፓኪስታን፣ የሶማሊያ እና የኢራን ዜጎችን አሳፍራ ከቱርክ ስለመነሳቷ ተገልጿል።

የተሰባበረ ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, Italian Red Cross

በየዓመቱ በብዛት ከአፍሪካ የሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ግጭት እና ድህነትን በመሸሽ በጀልባ ጣሊያን ለመድረስ ጥረት ያደርጋሉ።

ጀልባዋ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ውስጥ እየቀዘፈች ሳለ ከድንጋይ ጋር ከተጋጨች በኋላ ስለመስጠሟ ተገልጿል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የጀልባዋ ስብርባሪ ከጣሊያን ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ሲንሳፈፉ አሳይቷል።

ከጀልባ መስጠም በኋላ አንድ ግለሰብ ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጋር በተያያዝ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በአደጋው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፤ ለአደጋው ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

ቀኝ ዘመሙ የሜሎኒ አስተዳደር ስደተኞቸ ወደ ጣሊያን የሚያደርጉትን ጉዞ ከመነሻው በመግታት ወደ የጣሊያ የባሕር ዳርቻዎች እንዳይደርሱ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር።

አደጋውን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት እንዲሁም ፖፕ ፍራንሲስ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቫን ደር ላየን የአውሮፓን የፍልሰት ችግር ለመቅረፍ የአውሮፓ ኅብረት የጥገኝነት አጠያየቅ ሕግጋትን ለማሻሻል ጥረታችንን በእጥፍ መጨምር አለብን ብለዋል።

ፖፕ ፍራንሲስ ደግሞ ሕይወታቸውን ላጡት እና አድራሻቸው የጠፉትን በጸሎቴ አስባቸዋለሁ ብለዋል።

ከእአአ 2014 ጀምሮ አውሮፓ ለመድረስ በሚደረጉ ጥረቶች በሜዲትራንያን ባሕር ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል አልያም የደረሱበት አይታወቅም።